መጋቢት 17/2013(ዋልታ) – የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች፣ ሶማሌና የአፋር ክልሎች በትግራይ ክልል ድጋፍ ለሚሹ የህብረተሰብ ክፍሎች የገንዘብና የቁሳቁስ ድጋፍ አደረጉ፡፡
የደቡብ ክልል 20 ሚሊየን ብርና 2 ሁለት አምቡላንሶችን፤ የአፋር ክልል 13 ሚሊየን በጥሬ ገንዘብ 1 ሚሊየን 300 ሺህ ብር የሚያወጣ መድሀኒትና አንድ አምቡላንስ በጥቅሉ 18 ሚሊየን ብር፤ የሶማሌ ክልል የ20 ሚሊየን ብር ድጋፍ አድርገዋል፡፡
የደቡብ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ እርስቱ ይርዳ እንደገለጹት የትግራይ ህዝብ ለሀገራችን ደማቅ ታሪክ ጽፈው ያለፉ ጀግኖች መፍጠር የቻለ በመሆኑ ክብር ይገባዋል ብለዋል፡፡ በክልሉ ከዚህ ቀደም የተፈጠረውን ያለፈ ታሪክ በመተው የክልሉን ህዝብ ወደ ተሻለ ደረጃ ማሳደግ ላይ ሊተኮር ይገባልም ብለዋል፡፡
የትግራይን ህዝብ መልሶ ለማቋቋም የተጀመረው ድጋፍ ተጠናክሮ ይቀጥላልም ሲሉ ነው ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ የተናገሩት፡፡ ክልሉን ለማረጋጋት የህይወት መስዋዕትነት ለከፈሉ የጸጥታ አካላት ምስጋና አቅርበዋል፡፡
የአፋር ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አወል አርባ በበኩላቸው የክልሉን ህዝብ እና መንግሥት በመወከል ድጋፍ ባደረጉበት ወቅት እንደገለጹት በትግራይ ክልል በተፈጠረው የጸጥታ ችግር የአፋርም ክልል ቀጥተኛ ተጎጂ ነው ብለዋል፡፡
በተለይ በህግ ማስከበሩ ወቅት በነበረው ችግር የግብይት ስርአቱ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ማሳረፉን በማሳያነት ጠቅሰዋል፡፡
ትግራይን ወደነበረችበት መመለስ ብቻ ሳይሆን ከዚያም በላይ ከፍ ለማድረግ እንሰራለን ብለዋል፡፡ ራስን ማሸነፍ ጀግንነት ነው ያሉት አቶ አወል መሪዎች ራሳቸውን ማሸነፍ ቢችሉ ኖሮ ትግራይ ለዚህ አትበቃም ነበር ሲሉ ጠቁመዋል፡፡
በተመሳሳይም የሱማሌ ክልል ምክትል ረረዕሰ መስተዳደር አቶ ሙስጠፌ መሀመድ ለትግራይ ህዝብ ታላቅ አክብሮት እንዳላቸው ጠቅሰው በቀጣይም የህዝብ ለህዝብ ትስስር ለማድረግ በትኩረት ይሰራልም ብለዋል፡፡ አሁን የተደረገው ድጋፍ ቀጣይነት እንደሚኖረውም አስረድተዋል፡፡
የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ዋና ስራ አስፈፃሚ ዶ/ር ሙሉ ነጋ ድጋፉን በተረከቡበት ወቅት እንደገለጹት በትግራይ ክልል ባጋጠመው የጸጥታ ችግር በክልሉ የመሠረተ ልማቶች ውድመት የዜጎች መፈናቀል እና መሰል ችግሮች ተጋላጭ እንዲሆን ምክንያት ሆኗል ብለዋል፡፡
ዶክተር ሙሉ የደቡብ የአፋር እና የሱማሌ ክልል ህዝብ እና መንግሥት ላደረጉት ድጋፍ ምስጋና ማቅረባቸውን ከደቡብ ክልል መንግስት ኮሙዩኒኬሽን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡