በትግራይ ክልል 135 ዓለም አቀፍ ርዳታ ሰጪ ድርጅቶች ቢኖሩም በቂ ድጋፍ እያደረጉ አለመሆናቸው ተገለጸ

በትግራይ ክልል 135 ዓለም አቀፍ ርዳታ ሰጪ ድርጅቶች ቢኖሩም የሚያደርጉት ድጋፍ አነስተኛ መሆኑን የጊዝያዊ አስተዳደሩ የመንግስት ኮምኒኬሽን ቢሮ ገለጸ።

የቢሮው ኃላፊ ወይዘሮ እቴነሽ ንጉሤ የተወሰኑ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ኣልሚ ምግቦችንና ምግብ ነክ ያልሆኑ ግብአቶችን እያበረከቱ ቢሆንም ከእነሱ ከሚጠበቀው አንጻር ዝቅተኛ ነው ብለዋል።

የአለም የምግብ ፕሮግራም እና ቀይ መስቀል የመሳሰሉ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች እገዛ እያደረጉ ቢሆንም፣ በክልሉ ከገቡት ርዳታ ሰጪ ድርጅቶች ቁጥርና ከደረሰው ጉዳት አንፃር ሲታይ አሁን ካለው ድጋፋቸው በላይ ርዳታ መስጠት ይጠበቅባቸው ነበር ሲሉ ገልጸዋል፡፡

መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች እርዳታ በማከፋፋል ሂደት የሚያጋጥሙ ችግሮችን በመፍታት በቀጣይ ህፃናት ላይ ትኩረት በማድረግ ኣልሚ ምግብ እንዲሰጡ ቃል ገብተዋል ያሉት ወይዘሮ እቴነሽ፣ በቀጣይም ቃላቸውን ይጠብቃሉ ብለን ተስፋ እናደርጋለን ብለዋል፡፡

በአሁኑ ሰአት ያሉት ተፈናቃዮች የሚስፈልጋቸው አስቸኳይ እርዳታ በቀጥታ ሊመገቡት የሚችሉትን የተዘጋጁ ምግቦችን እንደሆነ ጠቅሰው፤ ለተፈናቃዮቹ የሚሆን መጠለያ ከመንግስት ከሚሰጥ በተጨማሪ በሃገር ውስጥ እና በውጭ ያሉት የትግራይ ተወላጆች ሆነ ኢትዮጵያውያን እገዛ እንዲያረጉ መጠየቃቸውን የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ዘግቧል፡፡

የትግራይ ክልል ሰብአዊ ድጋፍ 70 በመቶ በመንግስት የተሸፈነ ሲሆን፣ ከ135 በላይ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች በክልሉ እርዳታ ለመስጠት ቢገቡም የሚሰሩት ስራ በቂ አይደለም ነው የተባለው፡፡ መንግስት ብቻውን ለ4 ነጥብ 2 ሚሊየን ዜጎች ሰብኣዊ እርዳታ ማቅረቡ ይታወቃል፡፡