በንግድ ማጭበርበርና ኮንትሮባንድ ከ50 ቢሊየን ብር በላይ ማዳን መቻሉ ተገለጸ

ሐምሌ 25/2014 (ዋልታ) በንግድ ማጭበርበርና በኮንትሮባንድ መንግሥት ሊያጣው የነበረን ከ50 ቢሊየን ብር በላይ ማዳን መቻሉን የገቢዎች ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

የገቢዎች ሚኒስቴርና የጉምሩክ ኮሚሽን ከፍተኛ አመራሮች የተቋሙን የ2014 በጀት ዓመት እቅድ አፈፃፀም ገምግመዋል፡፡

በግምገማ መድረኩም የጉምሩክ ኮሚሽን በ2014 በጀት ዓመት በንግድ ማጭበርበርና በኮንትሮባንድ መከላከል በሰራው ጠንካራ የቁጥጥር ሥራ መንግሥት ሊያጣው የነበረን 50 ቢሊየን 46ሚሊየን 954 ሺሕ 335 ብር 57 ሳንቲም ማዳን መቻሉ ተገልጿል፡፡

አፈፃፀሙ ከ2013 በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀርም የ13 ነጥብ 3 ቢሊየን ብር ወይም 36 ነጥብ 28 በመቶ ብልጫ እንዳለው ተጠቁሟል፡፡

ማዳን ከተቻለው ገንዘብ ውስጥም በኢንተለጀንስ ሥራዎች 1ነጥብ 6 ቢሊየን፣ በድንገተኛ ፍተሻ 843 ነጥብ 82 ሚሊየን፣ በገቢ ኮንትሮባንድ ቁጥጥር 4 ነጥብ 284 ቢሊየን፣ በወጪ ኮንትሮባንድ ቁጥጥር 836 ነጥብ 64 ሚሊየን፣ ከድህረ እቃ አወጣጥ ኦዲት 9 ነጥብ 465 ቢሊየን፣ የቀረጥ ነፃ መብት አጠቃቀምን በመቆጣጠር 530 ነጥብ 81 ሚሊየን እና ቀሪው 33 ነጥብ 2 ቢሊየን ብር በመደበኛ ፍተሻ ሥራ ማዳን የተቻለ መሆኑም ተጠቅሷል፡፡

በእቅድ ግምገማው ወቅት የገቢዎች ሚኒስትር ላቀ አያሌው በንግድ ማጭበርበርና ኮንትሮባንድ መከላከል ሥራዎች ላይ ጉልህ ተሳትፎ ያደረጉ አካላትን ማመስገናቸውን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡