በአለም ትልቁ የክትባት ማምረቻ የሴረም ተቋም በተነሳ የእሳት አደጋ የሰዎች ህይወት አለፈ

 

የክትባት ማምረቻ ፋብሪካው የሚገኘው በምዕራቧ ህንድ፣ ፕሩን ግዛት ነው የእሳት አደጋው የተነሳው በግንባታ ላይ ባለው የሴረም ተቋም ክፍል ነው።

በትናንትናው ዕለት ከሰዓት የተነሳው እሳትም በተቋሙ አንደኛው የህንፃ ክፍል ላይ ጉዳት ቢያደርስም ክትባቶቹ ጉዳት እንደማይደርስባቸው ኩባንያው አረጋግጧል።

የእሳት አደጋው ምክንያት እስካሁን ግልፅ አይደለም።

አደጋው ከጥቂት ጊዜያት በኋላ በቁጥጥር ስር ቢውልም የከተማይቱ ከንቲባ የአምስት ሰዎች ህይወት አልፏል ብለዋል።

“በጣም የሚያሳዝን ዜና ሰምተናል። በማዕከላችን የተነሳው የእሳት አደጋ የሰዎች ህይወት መቅጠፉን ተረድተናል” በማለትም የሴረም ተቋም ዋና ስራ አስፈፃሚ አዳር ፑናዋላ በትዊተር ገፃቸው አስፍረዋል።

“በሁኔታው ጥልቅ ሃዘን ተሰምቶናል። በአደጋው ቤተሰብ፣ ወዳጅ ዘመዶቻቸውን ላጡ መፅናናትን እንመኛለን” በማለትም ስራ አስፈፃሚው መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።

አዳር የእሳት አደጋው በኦክስፎርዱ- አስራ ዜኔካ ክትባቶች ወይም በአገሬው ስም ኮቪሽልድ ምርት ላይ ምንም አይነት ተፅእኖ አያሳርፍም ብለዋል።

“በርካታ የማምረቻ ህንፃዎች አሉን ከዚህም በተጨማሪ ለንደዚህ አይነት አደጋዎችም ተቀማጭ አለን” ብለዋል።

ኮቪሽልድ በህንድ መንግሥት ፈቃድ ካገኙ ሁለት ክትባቶች አንዱ ነው። ህንድ ዜጎቿን የመከተብ ፕሮግራሟን ባለፈው ሳምንት ጀምራለች።

እስከ ነሐሴ ወር ባለውም ድረስ 300 ሚሊዮን ዜጎቿን የመከተብ እቅድን ሰንቃለች።

በርካታ መካከለኛና ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው አገራት የኦክስፎርዱን አስትራ ዜኔካ ክትባትን በሚያመርተው የሴረም ተቋምን እየተጠባበቁ ይገኛሉ።

በአለም አቀፍ ደረጃ በወረርሽኙ ከተጠቁት አገሮች አንዷ የሆነችው ህንድ ከአሜሪካ በመከተልም የሁለተኛነትን ስፍራ ይዛለች።

ወረርሽኙ ከተከሰተ ጀምሮ 10.6 ሚሊዮን ዜጎቿ በቫይረሱ የተያዙ ሲሆን 153 ሺህ ዜጎቿንም በቫይረሱ አጥታለች፡፡
(ምንጭ፡- ቢቢሲ)