በአማራ ክልል ለትምህርት ተቋማት ከ11 ቢሊዮን ብር በላይ ያስፈልጋል

ታኅሣሥ 3/2014 (ዋልታ) በአማራ ክልል በአሸባሪው ሕወሓት ቡድን የወደሙ የትምህርት ተቋማትን መልሶ ለማቋቋም ከ11 ቢሊዮን ብር በላይ እንደሚያስፈልግ ተገለፀ፡፡
በትምህርት ሚኒስትሩ ብርሃኑ ነጋ (ፕ/ር) የተመራ ልዑክ በሰሜን ወሎ ዞን መቄት ወረዳ በአሸባሪው የሕወሓት ቡድን የወደሙና ጉዳት የደረሰባቸውን ትምህርት ቤቶች ተመልክቷል፡፡
ልዑኩ የትምህርት ቤቶቹ መሰረተ ልማቶች መውደሚቸውን፣ የመማሪያ ፕላዝማዎች መዘረፋቸውን፣ ኮምፒውተርና የተለያዩ የትምህርት ቁሳቁስ ዘረፋና ውድመት እንደተፈጸመባቸው እና ትምህርት ቤቶች በከባድ መሳሪያ መደብደባቸውን ተመልክቷል፡፡
የትምህርት ሚኒስትሩ አሸባሪው ወራሪ ቡድን ትምህርት ቤቶችን ከመዝረፉ ባለፈ ድጋሚ አገልግሎት እንዳይሰጡ በማሰብ ማውደሙ የጨካኝነትና የክፋተኝነት ጥግ ማሳየቱን ተናግረዋል፡፡
ሚኒስትሩ በሽብር ቡድኑ ዘረፋና ውድመት የተፈጸመባቸውን ትምህርት ቤቶች መልሶ ለማቋቋም እየተሠራ መሆኑንም ገልፀዋል።
የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ማተብ ታፈረ (ዶ/ር) የሽብር ቡድኑ በአማራ ክልል ከ4 ሺሕ በላይ ትምህርት ቤቶች ላይ ውድመት ማድረሱን ገልጸዋል።
ከትምህርት ሚኒስቴር ጋር በመተባበር መልሶ ግንባታዎች በአጭር ጊዜ እንደሚሠራም መግለጻቸውን ከትምህርት ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመላክታል፡