በአማራ ክልል ሰላምና መረጋጋት እንዲመጣ በተወሰደው እርምጃ በአብዛኛው አካባቢዎች ሰላም ሰፍኗል – የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት


ጥቅምት 22/2016 (አዲስ ዋልታ) በአማራ ክልል የተፈጠረውን የፀጥታ ችግር በተመለከተ በክልሉ ሰላምና መረጋጋት እንዲመጣ በተወሰደው እርምጃ በአብዛኛው አካባቢዎች ሰላም ማስፈን እንደተቻለ የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ገለጸ።

ራሱን በፋኖ ስም የሚጠራው ፅንፈኛ ቡድን የአማራ ህዝብ ጥያቄን ሽፋን በማድረግ ኢ-ህገመንግስታዊ አካሄድን በመከተል በኃይልና በነፍጥ፣ በረብሻና በግርግር በመታገዝ በመጀመሪያ አማራ ክልልን ከዛም የፌደራል ሥርዓቱን በማፍረስ የራሱን እኩይ ኢኮኖሚያ እና ፖለቲካዊ ፍላጎቶች ለማሳካት አልሞ እንደነበር የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር) ገልጸዋል፡፡

በክልሉ ሰላምና መረጋጋት እንዲመጣ በተወሰደው እርምጃ በአብዛኛው አካባቢዎች ሰላም ማስፈን መቻሉን የገለጹት ሚኒስትሩ ቡድኑ የደቀነውን አደጋ ለመቀልበስ በወቅቱ መደበኛ በሆነ ህግ ማስከበር እንደማይቻል በመረጋገጡ መንግስት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በማውጣት እና የአስቸኳይ ጊዜ ኮማንድ ፖስት ጠቅላይ መምሪያ እዝ በማደራጀት ወደ ተግባር መግባቱንም አስታውሰዋል።

የአስቸኳይ ጊዜ መምሪያ እዙም በልዩ ልዩ አደረጃጀቶች ተደራጅቶ እና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር መግባባት ላይ ተደርሶ ወደ ተግባር ተገብቷል ነው ያሉት፡፡

በዚህም ተጨባጭ ውጤት ማምጣት ተችሏል ያሉት ሚኒስትሩ የአማራ ክልል አሁናዊ ሁኔታም ለመፍረስ ተቃርቦ የነበረውን ክልል ከመፍረስ መታደግ መቻሉን አመልክተዋል።

በሌላ በኩል በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች በሰው ሰራሽና ተፈጥሯዊ መነሻ የምግብ እጥረት እንዳጋጠመ የተገለፀ ሲሆን ለዚህም ምክንያት በአንዳንድ አካባቢዎች ወቅቱን ያልጠበቅ ዝናብ እና በሌሎች አካቢዎችም በነበረው የሰላምና መረጋጋት እጦት አማካይነት የተከሰተ መሆኑ ተገልጿል::

ይሁንና በአካባቢው ያሉ ዜጎችን ያጋጠመውን የምግብ እጥረት ለመፍታት በርካታ ስራዎች እየተሰሩ መሆናቸው ተመላክቷል::

ከዚህ መካከልም በዝናብ እጥረት ያጋጠመ ድርቅን ለመከላከል የመስኖና ተያያዥ ስራዎች እየተሰሩ መሆናቸውንና የህዝቦችንም ከከፋ ችግር ለመታደግ ድጋፎች እየተደረጉ መሆናቸውን ሚኒስትሩ በመግለጫቸው ገልጸዋል::

እስካሁንም በሰው ሰራሽና ተፈጥሯዊ ክስተቶች የምግብ እጥረት ባጋጠማቸው አካባቢዎች አካባቢዎች 6.4 ቢሊየን ብር ግምት ያለው ድጋፍ መደረጉ ተመላክቷል።

በሔብሮን ዋልታው