በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ እና ኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞኖች የአብሮነትና የሰላም ሥነ-ሥርዓት እየተካሄደ ነው

ግንቦት 25/2013 (ዋልታ) – የጸጥታ ችግር ተከስቶባቸው በነበሩት የአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ እና ኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞኖች የህዝብ ለህዝብ ትስስርን የሚያጠናክር የአብሮነትና የሰላም ሥነ-ሥርዓት እየተካሄደ ነው።

የአብሮነትና የሰላም ሥነ-ሥርዓቱ በከሚሴ ከተማ ደዋ ጨፋ ወረዳ ተረፍ ቀበሌ አስተዳደር እየተካሄደ ሲሆን፣ ሰላምንና አብሮነትን ያስተሳስራል ተብሎ ይጠበቃል።

ከጥቂት ጊዜያት በፊት የጸጥታ መደፍረስና ከፍተኛ ችግሮች ደርሰውበት የነበረውን የሰሜን ሸዋ ዞንና የኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞንን ወደ ቀድሞ እንቅስቃሴ በተጠናከረ ሁኔታ ለመመለስና የተፈናቀሉ ወገኖቻችን ለመደገፍ የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ ይገኛል።

በሥነ-ሥርዓቱ ላይ በአካባቢው የተቋቋመው የጸጥታ ግብርኃይል ዋና አስተባባሪ ሌተናል ጄኔራል ደስታ አቢቼን ጨምሮ የአካባቢው ነዋሪዎች እና የሁለቱ ዞኖችና የመከላከያ ሠራዊት ከፍተኛ አመራሮች ተገኝተዋል።

ከነዚህ ተግባራት መካከል የአካባቢውን ነዋሪዎች አንድነትና ወንድማማችነትን የሚያጠናክርው የአብሮነትና የሰላም ሥነ-ሥርዓት በዛሬው እለት በአካባቢው ባህል መሠረት እየተካሄደ ይገኛል።

በሐይማኖት አባቶችና በሀገር ሽማግሌዎች መሪነት እየተከናወነ የሚገኘው ሥነ-ሥርዓቱ ከዚህ ቀደም የተከሰቱ ችግሮች ዳግም እንዳይከሰቱ ለማድረግና ወንጀለኞችን ለማጋለጥ ያለመ መሆኑን የኢዜአ ዘገባ ያመለክታል።