በአማራ ክልል በሕወሓት የወደሙ ትምህርት ቤቶችን መልሶ ሥራ ለማስጀመር ከ11 ቢሊየን ብር በላይ ያስፈልጋል ተባለ

ታኅሣሥ 1/2014 (ዋልታ) በአማራ ክልል በአሸባሪው በሕወሓት የወደሙ ከ4 ሺሕ የሚበልጡ የትምህርት ተቋማትን መልሶ ሥራ ለማስጀመር ከ11 ቢሊዮን ብር በላይ እንደሚያስፈልግ ተገለጸ፡፡

አሸባሪው ሕወሓት በክልሉ ያወደማቸው የትምህርት ተቋማትን መልሶ ለመገንባት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ያተኮረ ውይይት በባህር ዳር ከተማ እየተካሄደ ነው።

የትምህርት ሚኒስትር ብርሀኑ ነጋ (ፕሮፌሰር) በውይይቱ ላይ ባደረጉት ንግግር አሸባሪው ሕወሓት የነገ አገር ተረካቢ ትውልድ በሚቀረፅባቸው የትምህርት ተቋማት ላይ ከፍተኛ ውድመት አድርሷል ብለዋል።

ባለድርሻ አካላትን በማስተባበር የወደሙና የፈረራሱ የትምህርት ተቋማትን መልሶ በመገንባትና በመጠገን ሥራ እንዲጀምሩ ለማድረግ መንግስት በቁርጠኝነት እንደሚሰራ ተናግረዋል።

የትምህርት ተቋማትን መልሶ ሥራ ለማስጀመር በሚደረገው ርብርብ የሁሉም ባለድርሻ አካላት ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑንም ነው ሚኒስትሩ ያመለከቱት።

“የፈረሱት ትምህርት ቤቶች የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ ለሚደረገው ጥረት እንቅፋት እንዳይሆኑ የጥራት ደረጃቸውን በጠበቀ መንገድ ገንብቶ ለአልግሎት ማብቃት የግድ ነው” ብለዋል።

“ተቋማቱ በጥራት ተገንብተው ለአገልግሎት ካልበቁ የአሸባሪውን ዕቅድ ማሳካት ስለሆነ የመልሶ ግንባታና ማደረጃቱ ሥራ በልዩ ትኩረት ይከናወናል” ሲሉም አክለዋል።

የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ማተቤ ታፈረ (ዶ/ር) በበኩላቸው እንዳሉት  አሸባሪው የሕወሓት ቡድን በወረራ ይዟቸው በቆዩ የክልሉ አካባቢዎች ከ4ሺህ የሚበልጡ የትምህርት ተቋማትን አውድሟል።

ትምህርት ቤቶች ገንብቶና ጠግኖ መልሶ የመማር ማስተማር ስራውን ለማስጀመር ከ11 ቢሊየን ብር በላይ እንደሚያስፈልግ መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

ኃላፊው እንዳሉት ትምህርት ቤቶቹ በመውደማቸው ከ1 ነጥብ 8 ሚሊየን በላይ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ እንዲሁም 116 ሺህ መምህራን ከሥራ ውጭ ሆነዋል።

የወደሙ የትምህርት ተቋማትን ለመገንባትና ቁሳቁስ አሟልቶ ወደ ነበሩበት ለመመለስ ሁሉም ባለድርሻ አካላት አስፈላጊውን ድጋፍና እገዛ እንዲያደርጉ ዶክተር ማተቤ ጥሪ አቅርበዋል።