በአማራ ክልል በሩዝ ሰብል የሚለማው መሬት እየጨመረ መምጣቱ ተገለጸ


መስከረም 15/2016 (አዲስ ዋልታ) በአማራ ክልል የሩዝ ልማትን ለማስፋፋት በተደረገው ጥረት በሰብሉ የሚለማው መሬትና የሚገኘው ምርት እየጨመረ መምጣቱን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ።

በክልሉ በ2015/2016 የምርት ዘመን በሩዝ ሰብል ከለማው መሬት 5 ነጥብ 4 ሚሊዮን ኩንታል ምርት እንደሚጠበቅ ተገልጿል።

በቢሮው የሩዝ ሰብል ልማት አስተባባሪ እንዬ አሰፋ ምርቱ የሚጠበቀው የሩዝ ልማቱ በሚካሔድባቸው ሩዝ አብቃይ 17 ወረዳዎች ውስጥ ከለማው 83 ሺሕ 650 ሄክታር መሬት ላይ መሆኑን ገልጸዋል።

ክንውኑ ካለፈው ተመሳሳይ የምርት ዘመን ጋር ሲነፃፀር በ22 ሺሕ ሄክታር በምርት ደግሞ ከ2 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ብልጫ እንደሚኖረው አመልክተዋል።

ይህም በሰብሉ የሚለማው መሬትና የሚገኘው ምርት እየጨመረ መምጣቱን እንደሚያመለክት ጠቅሰው የፎገራ ብሄራዊ የሩዝ ምርምርና ስልጠና ማዕከልና ሌሎች ድርጅቶች በሚያቀርቡት የተሻሻለ ዝርያ አርሶ አደሩ የምግብ ዋስትናውን እንዲያረጋጥና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነቱንም እንዲያሳድግ ማገዙን መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

ባለፈው ዓመት በክልሉ በሩዝ ሰብል ከለማው 61 ሺሕ 497 ሄክታር መሬት ከ3 ነጥብ 2 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት መገኘቱንና በክልሉ ለሩዝ ሰብል ልማት ተስማሚ የሆነ ከአንድ ሚሊዮን ሄክታር በላይ መሬት መኖሩን ከቢሮው የተገኘው መረጃ ያመለክታል።