በአማራ ክልል በኢንዱስትሪው ዘርፍ የተሰማሩ ባለሀብቶችን ለማበረታታት ድጋፍ ይደረጋል – ይልቃል ከፋለ (ዶ/ር)

ይልቃል ከፋለ (ዶ/ር)

ጥር 5/2015 (ዋልታ) በአማራ ክልል በአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ የተሰማሩ ባለሀብቶችን ለማበረታታት ተገቢው ድጋፍ እንደሚደረግ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ይልቃል ከፋለ (ዶ/ር) ተናገሩ።

በደብረ ብርሃን ከተማ በአንድ ቢሊዮን ብር ወጪ የተገነባ “ዜማ” የተሰኘ የጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካ ዛሬ በርዕሰ መስተዳድሩ ተመርቆ ስራ ጀምሯል።

በምርቃት ሥነ-ሥርዓቱ ላይ ርዕሰ መስተዳድሩ ባደረጉት ንግግር እንደነዚህ ያሉ ግዙፍ ፋብሪካዎች መገንባታቸው የውጭ ምንዛሬን ግኝት ለማስፋት ፋይዳቸው የጎላ መሆኑን ገልጸዋል።

የደብረ ብርሃን ከተማ አስተዳደር ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት መምሪያ ኃላፊ ብርሀን ገብረህይወት በበኩላቸው የኢንቨስትመንት ፈቃድ አውጥተው በፍጥነት ወደ ተግባር ለሚሸጋገሩ ባለሃብቶች አስተዳደሩ ልዩ ድጋፍ እንደሚያደርግ አስታውቀዋል።

ዘንድሮ በተለያዩ የኢንቨስትመንት አማራጮች ለሚሳተፉ ባለሃብቶችም ከ2 ሺሕ ሄክታር በላይ መሬት መዘጋጀቱን ጠቁመዋል።

ዛሬ የተመረቀው ፋብሪካ በቅርቡ እንደሚመረቁ ከሚጠበቁ 24 ኢንዱስትሪዎች መካከል አንዱ መሆኑን ጠቅሰዋል።

የውጭና ሀገር ውስጥ ባለሀብቶች ራሳቸውንና የአካባቢውን ህዝብ ለመጥቀም መጥተው እንዲሰሩም ጥሪ አቅርበዋል።

የ”ዜማ” ጨርቃጨረቅ ፋብሪካ ባለቤት አሽርቅ ሲራጅ ፋብሪካው የተገነባው በአንድ ቢሊዮን ብር ወጪ መሆኑን ገልጸው አሁን ላይ ማምረት መጀመሩንና ለ300 ሰዎች የስራ እድል እንደፈጠረ አመልክተዋል፡፡ በቀጣይም ለሌሎች ወገኖች ተጨማሪ የስራ እድል እንደሚያመቻቹ ተናግረዋል።

ርዕሰ መስተዳድሩ በደብረ ብርሀን ከተማ እየተከናውኑ ያሉ ሌሎች የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴዎችን ተዘዋውረው መጎብኘታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡