በአማራ ክልል የመንግሥት ተቋማት መደበኛ ሥራዎቻቸውን እንዲጀምሩ ውሳኔ ተላለፈ

ግዛቸው ሙሉነህ

ታኅሣሥ 14/2014 (ዋልታ) በአማራ ክልል የመንግሥት ተቋማት መደበኛ ሥራዎቻቸውን እንዲጀምሩ ውሳኔ መተላለፉን የክልሉ የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ አስታወቀ።

የክልሉ መስተዳድር ምክር ቤት በክልሉ ወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ትናንት ተወያይቶ አቅጣጫዎችን ማስቀመጡን እና በተወሰኑ ጉዳዮች ዙሪያ ማሻሻያ ማድረጉን የክልሉ መንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ ግዛቸው ሙሉነህ ተናግረዋል።

የክልሉ መስተዳድር ምክር ቤት በውይይቱ አሁን የተገኘውን አንፃራዊ ድል ከግምት ውስጥ በማስገባት ተቋማት መደበኛ ሥራዎቻቸውን እንዲጀምሩ እና በየደረጃው ከሚገኙ ሠራተኞቻቸው ጋር በመወያየት እቅዳቸውን አሻሽለው እንዲጀምሩ ወስኗል።

የተፈናቀሉ የመንግሥት ሠራተኞች ወደ ሥራቸው እንዲመለሱ፣ የኅልውና ዘመቻውን ለመደገፍ የወጡ የመንግሥት ሠራተኞች ተመልሰው ከመደበኛ ሥራቸው ጎን የኅልውና ዘመቻውን እንዲደግፉም ውሳኔ ተላልፏል።

በክተት ጥሪው የክልሉ መንግሥት ተቋማት መደበኛ ሥራዎቻቸውን አቁመው ወደ ኅልውና ዘመቻው እንዲዞሩ እና በጀታቸውም ለዚሁ ዓላማ እንዲውል አስገዳጅ ውሳኔ ተወስኖ ነበር።

ከቀበሌ እስከ ዞን የፈረሱ ተቋማትን አደራጅቶ ወደ ሥራ የማስገባቱ ሥራ እየተጠናቀቀ ነውም ተብሏል።

አብዛኛው አካባቢዎች ከሽብር ቡድኑ ነጻ መሆናቸውን ተከትሎ የአማራ ክልል መስተዳድር ምክር ቤት በተወሰኑ ጉዳዮች ላይ ማሻሻያ ማድረጉን ገልጿል።

አሸባሪው ሕወሓት በከፈተው ወረራ የክልሉ መንግሥት የክተት ጥሪ አስተላልፎ እንደነበር ያወሱት የክልሉ መንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ ግዛቸው ሙሉነህ የክተት ጥሪውን ተቀብለው በግንባር፣ በሎጀስቲክስ፣ በፕሮፖጋንዳ እና በደጀንነት ለተሳተፉት ሁሉ ምስጋና አቅርበዋል።

የክልሉን የጸጥታ ሁኔታ በሚመለከት የተወያየው የክልሉ ካቢኔ በሁሉም የክልሉ አካባቢዎች የ24 ስዓት የተጠናከረ የጥበቃ አገልግሎት እንዲደረግ አቅጣጫ አስቀምጧል።

በኬላዎች፣ መግቢያ እና መውጫ በሮች እና በተመረጡ አካባቢዎች ፍተሻው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የገለጹት ኃላፊው ሕዝቡ በተለይም ወጣቶች የየአካባቢያቸው የሰላም አርበኛ መሆን አለባቸው ብለዋል።

ስርቆት፣ ሥርዓት አልበኝነት፣ ዘረፋ እና የሕዝቡን ሰላም የሚነሱ ጉዳዮች ላይ ጥብቅ ቁጥጥር ይደረጋልም ነው ያሉት ኃላፊው። ድልን ምክንያት አድርጎ በየአካባቢው የሚደረግ ተኩስ ተገቢ አለመሆኑንም ገልጸዋል።

የክልሉ ሕዝብ ላለፉት ስድስት ወራት ሰላም እና እንቅልፍ አጥቶ ቆይቷል ያሉት ኃላፊው የሕዝብን ሰላም የሚረብሹ አካላት ከድርጊታቸው እንዲታቀቡም አሳስበዋል።

እንደየአካባቢው ነባራዊ ሁኔታ የሚተገበረው የሰዓት እላፊ ገደብ ማሻሻያም ከዛሬ ጀምሮ ተግባራዊ ይደረጋል ተብሏል።

ሌላው የክልሉ መስተዳድር ምክር ቤት አቅጣጫ ካስቀመጠላቸው ጉዳዮች መካከል በቅርቡ የሚከበሩ ሕዝባዊ እና ሃይማኖታዊ በዓላትን የሚመለከት ነው።

በጦርነቱ ምክንያት የተጎዳውን የክልሉን ምጣኔሃብታዊ እንቅስቃሴ ለመደገፍ በዓላቱ ትልቅ ሚና አላቸው ያሉት የቢሮ ኃላፊው ጥሪ የተደረገላቸው የዲያስፖራው ማኅበረሰብም ወደ ክልሉ ይመጣሉ ብለዋል።

እንግዶችን ያለምንም የጸጥታ ስጋት አስተናግዶ ለመመለስ ሁሉም የጸጥታው ባለቤት መሆን አለበት ነው ያሉት።

ሕዝቡም የልደት በዓልን በላልይበላ እና ጥምቀትን በጎንደር በተረጋጋ ሁኔታ እንዲያከብር ቅድመ ዝግጅቶች ተጀምረዋል ብለዋል።

በአጠቃላይ የክልሉ መንግሥት መስተዳድር በመላው ኢትዮጵያዊያን የጋራ ርብርብ ለተገኘው ድል እውቅና ሰጥቶ ድሉ ዘላቂ የሚሆነው ተጎጂዎች ከጉዳታቸው ሲያገግሙ እና የሽብር ቡድኑ ሲጠፋ፣ አመለካከቱም ለመጨረሻ ጊዜ ሲከስም በመሆኑ ለቀጣይ ግዳጆች የተለመደ የጋራ ርብርብ እንደሚያስፈልግም አቅጣጫ አስቀምጧል ማለታቸውን አሚኮ ዘግቧል።