በአማራ ክልል የሚስተዋሉ የኢንቨስትመንት ችግሮች በፍጥነት እንዲሻሻሉ ማሳሰቢያ ተሰጠ

መጋቢት 27/2014 (ዋልታ) የአማራ ክልል ርዕሠ መስተዳድር ይልቃል ከፋለ (ዶ/ር) በክልሉ የሚስተዋሉ የኢንቨስትመንት ችግሮች በፍጥነት እንዲሻሻሉ አሳሰቡ፡፡

በክልሉ ለባለሀብቱ የሚሰጠው አገልግሎት ባለሀብቱን የሚያረካ ባለመሆኑ ችግሩን ለመፍታት በትኩረት መሠራት እንዳለበት የጠቆሙት ርዕሠ መስተዳድሩ በርካታ ባለሀብቶች የልማት ቦታ ቢሰጣቸውም የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት መወጣት አለመቻላቸውን አስገንዝበዋል።

ርዕሠ መስተዳድሩ ይህንን ያሉት የአማራ ክልል ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ በክልሉ የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ ዙሪያ ከባለሀብቶችና ከባለድርሻ አካላት ጋር በባሕር ዳር ዛሬ ባካሄደው ውይይት ላይ ነው።

ባለሃብቶችን የሚገጥሙ የኢንቨስትመንት ችግሮች በፍጥነት እንዲሻሻሉ መመሪያ በመስጠት ባለሃቶችም ለሕዝብ ቃል የገቡትን የሥራ እድል ፈጠራ በተግባር ማሳየት እንዳለባቸው አሳሰበዋል፡፡

የክልሉ መንግሥት ከባለሀብቱ ጋር በቅርበት እንደሚሰራ ጠቁመው ክልሉ በመስኖ ሊለማ የሚችል መሬት፣ የማዕድንና ሌሎች ሀብቶች ባለቤት መሆኑን መናገራቸውን የዘገበው አሚኮ ነው።

የአማራ ክልል ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ ኃላፊ እንድሪስ አብዱ በበኩላቸው ባለፉት ዓመታት የክልሉ መንግሥት ለኢንቨስትመንት ንቅናቄው ትኩረት ሰጥቶ ሲሠራ እንደቆየ ተናግረዋል።