በአማራ ክልል የኦሮሞ ብሔረሰብ ልዩ ዞን ከትሕነግ እና ሸኔ ጋር የተባበሩ አመራሮችን ከኃላፊነታቸው አነሳ

ታኅሣሥ 16/ 2014 (ዋልታ) የትሕነግ አሻባሪ ቡድን በአማራ ክልል የኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ልዩ ዞን ከሸኔ ኃይሎች ጋር ሆኖ በፈፀመው ወረራ በአሸባሪነት የተፈረጁትን የሁለቱ ቡድኖች የጥፋት ተልዕኮ ለማስፈፀም ሲንቀሳቀሱ የነበሩ አመራሮች ከኃላፊነታቸው እንዲነሱና በቁጥጥር ስር እንዲውሉ ተደረገ።
የልዩ ዞኑ ምክር ቤት አስቸኳይ ስብሰባ በመጥራት በጉዳዩ ላይ ከተወያየ በኋላ በርካታ የዞኑ አመራሮችን ከኃላፊነት በማንሳት በአዲስ ተክቷል።
ከዚህም ባሻገርም ከሽብር ቡድኖቹ ጋር ያበሩ ኣካላትም በሕግ ቁጥጥር ስር ውለዋል ተብሏል።
አዲስ የተሾሙት የልዩ ዞኑ አመራሮች ማኅበረሰቡን በማደራጀት የአካባቢውን ሰላም በዘላቂነት ማስጠበቅ እና የዞኑ ነዋሪዎች ሽብርተኞቹ የትሕነግ እና ሸኔ ቡድኖች ካደርሱባቸው የምጣኔሃብትና ማኅበራዊ ችግሮች እንዲያገግሙ ማድረግ ቀዳሚ ተግባራቸው እንዲሆን ምክር ቤቱ አሳስቧል።
በሌላ መልኩ በልዩ ዞኑ በአሸባሪ ቡድኖቹ ምክንያት ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉ ዜጎች የመደገፍና ተቋርጠው የነበሩ የመንግሥት የአገልግሎት ተቋማት ዳግም ስራ የማስጀመር ሥራ እየተከናወነ መሆኑን የኢብኮ ዘገባ ያሳያል።