በአማራ ክልል 11.6 ሚሊዮን ሕዝብ የምግብ እርዳታ እንደሚያስፈልገው የክልሉ መንግሥት አስታወቀ

መጋቢት 8/2014 (ዋልታ) በአማራ ክልል 11 ነጥብ 6 ሚሊዮን ሕዝብ የምግብ እርዳታ እንደሚያስፈልገው የክልሉ መንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ አስታወቀ።
የቢሮ ኃላፊ ግዛቸው ሙሉነህ በክልሉ በተለያየ ጊዜ የተፈናቀሉ እንዲሁም ጦርነቱ በፈጠረው ችግር ሳቢያ ወደ 11 ነጥብ 6 ሚሊዮን የሚጠጉ ዜጎች የምግብ እርዳታ ያስፈልጋቸዋል ብለዋል፡፡
በአሁን ወቅትም ከተለያዩ አካባቢዎች የተፈናቀሉ 263 ሺሕ ዜጎች በክልሉ ውስጥ ይገኛሉ ያሉት ኃላፊው የተፈናቀለ ብቻ ሳይሆን በጦርነቱ ቀጣና ውስጥ ያላመረተና ችግር ውስጥ የገባ እርዳታ የሚፈልግ 11 ነጥብ 6 ሚሊዮን ሕዝብ መኖሩን ገልጸዋል፡፡ ይህም በምጣኔ ሀብት ብቻ ሳይሆን ዘርፈ ብዙ ጉዳት እንዳለውና ክልሉም በዚህ ደረጃ ዋጋ እየከፈለ መሆኑን አስታውቀዋል።
በተለያየ መንገድ ከዋግኅምራ አዋሳኝ አካባቢዎች፣ ከአላማጣና ከኮረም ተፈናቅለው ወደ ቆቦ የመጡ በተመሳሳይ በሰሜን በኩል ተፈናቅለው ወደ ደባርቅ የመጡ እንዳሉ ጠቅሰዋል።
በልዩ ልዩ ችግሮች ምክንያት ከክልሉ ውጭ የሚኖሩ ዜጎች ተፈናቅለው ወደ ክልሉ የመጡበት አጋጣሚ እንዳለም ጠቁመዋል።
ተፈናቃዮች ብዙ ሀብት ንብረታቸው ተዘርፎና ተቃጥሎ ጉዳት እንደደረሰባቸው ጠቅሰው ይህ የክልሉን ልማት ምጣኔ ሃብታዊና ማኅበራዊ እንቅስቃሴ ችግር እንዲገጥመው ምክንያት መሆኑንም አስረድተዋል።
ጫናው እንዳይበረታ ለማድረግ ከጎረቤት ክልሎች ጋር ተመካክሮ በመሥራት ቀጣናውን ሰላም ማድረግ እንደሚገባ ያመለከቱት ኃላፊው ለሰላም መድፍረስና ለዜጎች መፈናቀል መነሻ የሆኑ ጉዳዮችን በጋራ በመመካከር መሥራት ትልቁ መፍትሔ እንደሆነና ለዚህም ሁሉንም ሰው የመፍትሔው አካል ማድረግ እንደሚገባ መግለፃቸውን ኢፕድ ዘግቧል፡፡