በአሜሪካ በኢትዮጵያውያን የተመሰረቱ አደረጃጀቶች በኢትዮጵያ ላይ እየተደረጉ ያሉ ጫናዎችን ለመመከት በቅንጅት እንደሚሰሩ አስታወቁ

ሰኔ 08/2013 (ዋልታ) – በመላው አሜሪካ የሚገኙ በኢትዮጵያውያን የተመሰረቱ የተለያዩ አደረጃጀቶች በኢትዮጵያ ላይ እየተደረጉ ያሉ ያልተገቡ ጫናዎችን ለመመከት በቅንጅት እንደሚሰሩ አስታውቀዋል።

ከሁሉም የአሜሪካ ግዛቶች የተውጣጡ በዳያስፖራ ኢትዮጵያውያን የተቋቋሙ ማህበራት እና የኮሚዩኒቲ አደረጃጀቶች ተወካዮች በተገኙበት የበይነ መረብ ውይይት ተካሂዷል።

በውይይቱ ወቅት በአሜሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር ፍጹም አረጋ ባስተላለፉት መልዕክት አደረጃጀቶች የኢትዮጵያ ድምጽ እንዲሰማ እያደረጉ ላለው አስተዋጽኦ አመስግነው፣ እየተደረገ ካለው ጫና አኳያ በቅንጅት መስራት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።

የየማህበራቱ ተወካዮችም በኢትዮጵያ ላይ የተከፈተው ያልተገባ ጫና እና የሃሰት ፕሮፖጋንዳ እስኪወገድ ድረስ ሁሉን አቀፍ እንቅስቃሴውን እንደሚቀጥሉ ቃል ገብተዋል።

በመላው አሜሪካ ለሚኖሩ ዳያስፖራ ወገኖችም በዚህ ታሪካዊ ወቅት ከኢትዮጵያ ጎን በመቆም አለኝታነታቸውን እንዲያሳዩ ጥሪ ማቅረባቸውን በዋሽንግተን የኢትዮጵያ ኢምባሲ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።