በአርሲ ዞን የእስልምና እምነት ተከታዮች ለቤተክርስቲያን ማሰሪያ 3 ሚሊዮን ብር ለገሱ

ሚያዝያ 28/2014 (ዋልታ) የአርሲ ዞን ሙኔሣ ወረዳ የእስልምና እምነት ተከታዮች ለኦርቶዶክስ ሃይማኖት ተከታዮች ቤተክርስቲያን ማሰሪያ 3 ሚሊዮን ብር እና 20 የቀንድ ከብቶች አሰባስበው አበርክተዋል።
በወረዳው የእስልምና እና የክርስትና እምነት ተከታዮች ለዘመናት በመከባበር እና በመቻቻል በፍቅር አብረው እየኖሩ መሆኑን የሁለቱ ሃይማኖቶች ተከታዮች ገልጸዋል።
የሁለቱም እምነት ተከታዮች አንዳቸው ለሌኛው በየተራ መስጂድ እና ቤተክርስቲያን ተባብረው እያሠሩ በክፉ እና በደጉ አብረው ቆመው እስከ አሁን ደርሰዋል።
የሁለቱ እምነት ተከታዮች አንዱ ለአንዱ ቤተ እምነት መሥራት የቆየ ከአባቶቻችን የወረስነው እሴት ስለሆነ እኛም ይህንኑ እያስቀጠልን ነው ብለዋል።
የሥርዓት ለውጥም ሆነ የፖለቲካ ችግር ሀገሪቷን በገጠማት ወቅት ምንም ዓይነት የሃይማኖት ግጭት በወረዳው ተከስቶ አያውቅም ነው ያሉት ነዋሪዎቹ፡፡
በወራዳችን ሃይማኖት የመቻቻል እና የአብሮነት ምንጭ እንጂ የግጭት መንሥኤ ሆኖ አያውቅምም ብለዋል።
የክርስትና እምነት ተከታዮች በበኩላቸው የሙስሊም ማኅበረሰብ ላደረጉላቸው ድጋፍ አመስግነው፣ ይህን የቆየ የአባቶቻችንን እሴት አጠናክረን እናስቀጥላለን ብለዋል።
የሙኔሣ ወረዳ አስተዳዳሪ አማን ሻቁሮ ደግሞ በወረዳዋ መቀመጫ ቀርሣ ከተማ የመጀመሪያው መስጅድ የተሠራው በክርስትና እምናት ተከታይ የሀገር ሽማግሌ መሆኑን አስታውሰዋል፡፡
የከተማው ትልቁ መስጅድ መርካዝ የሚበላውም በክርስትና እምነት ተከታዮች ትብብር የተሠራ ነው።
ይህ በየተራ ቤተ እምነት አንዱ ለአንዱ የመሥራት ባህልም ተጠናክሮ እንደቀጠለ ነው ማለታቸውን ኦቢኤን ዘግቧል።