በአሶሳ 85 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ሥር መዋል

ነሐሴ 26 /2013 (ዋልታ) – በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል አሶሳ ከተማ የጸጥታ ችግር ለመፍጠር በመንቀሳቀስ የተጠረጠሩ 85 ሰዎችን በቁጥጥር ሥር ማዋሉን ፖሊስ አስታወቀ፡፡
የከተማው ወጣቶች ፀረ ሰላም ኃይሎች ጥፋት እንዳያደርሱ ተደራጅተው ሰላም እያስጠበቁ መሆናቸው ተገልጿል፡፡
የከተማዋ ፖሊስ መምሪያ ኃላፊ ኮማንደር ቡሽራ አልቀሪብ ተጠርጣሪዎቹ የከተማውን የሰላምና ጸጥታ ሁኔታ አስተማማኝ ለማድረግ የተጣለውን የሰዓት እላፊ ገደብ ጥሰው ሲንቀሳቀሱ በመገኘታቸው ተይዘዋል ብለዋል።
ተጠርጣሪዎቹ በአገር መከላከያ ሰራዊት፣ በፌዴራል ፖሊስ፣ በክልሉ ልዩ ኃይልና በነዋሪዎች የተቀናጀ የጸጥታ አስከባሪ ኃይል አማካኝነት መሆኑን የገለጹት ኮማንደር ቡሽራ፤ ከተጠርጣሪዎቹ መካከል የአሸባሪው ህወሃት ርዝራዦች እንደሚገኙበት ጠቅሰዋል።
ከተጠርጣሪዎቹ መካከል የ53ቱ የባንክ ሂሳብ፣ ተሸከርካሪዎችና ሌሎች ንብረቶች በፍርድ ቤት ትዕዛዝ መታገዱን ለኢዜአ ተናግረዋል፡፡