ነሃሴ 14/2013 (ዋልታ) – በአሸባሪው ህወሓት ቡድን ተይዘው የነበሩ የንግድና የመኖሪያ ቤቶችን በማጣራት ተመልሰው የአገርን ልማት በሚያግዝ መልኩ ጥቅም ላይ እንዲውሉ የማድረግ ተግባር ተጠናክሮ መቀጠሉን የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን ዋና ዳይሬክተር ረሻድ ከማል ገለፁ፡፡
አቶ ረሻድ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ መንግሥት በህወሓት አሸባሪ ቡድን ያለአግባብ ተይዘው የነበሩ የንግድና የመኖሪያ ቤቶችን በማጣራት ልማቱን በሚደግፍ ተግባር ላይ ለማዋል እየሰራ ይገኛል፡፡
አሸባሪ ቡድኑ በሥልጣን ዘመኑ አንድም የልማትና መኖሪያ ቤት እንዳልገነባ የጠቆሙት ኃላፊው፤ ይልቁንም በተለያዩ መንገዶች ሲቀራመታቸው የኖሩ ቤቶች ለሽብር ተግባሩ የገቢ ምንጭነት ሲያውላቸው እንደነበር አመልክተዋል፡፡
የአሸባሪ ቡድኑ ድርጊት አገርን አሳልፎ ለውጭ ጠላት የሚሰጥ ተግባር ነው ያሉት አቶ ረሻድ፤ ድርጊቱ ለአገር ልማትና ለዴሞክራሲ ግንባታ ቆሜያለሁ ሲል ከኖረና የአገርን ፍሬ ከበላ አካል የማይጠበቅ እኩይ ተግባር እንደመሆኑ ሁሉም ኢትዮጵያዊ የአገር አንድነት እና ሉዓላዊነት አስጠብቆ ለማቆየት ድርሻውን ሊወጣ ይገባል ብለዋል፡፡