በአሸባሪው ህወሓት የወደሙ የኤሌክትሪክ መሰረተ ልማቶችን የመጠገን ሥራ ከፍተኛ ርብርብ እየተደረገበት ነው

ሞገስ መኮንን

ጥቅምት 17/2015 (ዋልታ) በአሸባሪው ህወሓት የወደሙ የኤሌክትሪክ መሰረተ ልማቶችን የመጠገን ሥራ ከፍተኛ ርብርብ እየተደረገበት መሆኑን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል አስታወቀ።

የኤሌክትሪክ ኃይል የኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር ሞገስ መኮንን እንደገለጹት በሰሜኑ ጦርነት አሸባሪው ህወሓት የመሰረተ ልማቶችን የማውደምና የመዝረፍ ሥራ በመፈፀሙ ከፍተኛ ኪሳራ አስከትሏል።

በተለይም በአማራና ትግራይ ክልሎች የኤሌክትሪክ መሰረተ-ልማቶችን በማውደሙ የመብራት አገልግሎት ተቋርጦ መቆየቱን አስታውሰዋል።

ጉዳትና ውድመት የደረሰበትን መሰረተ ልማት በመጠገን ዳግም አገልግሎት ለማስጀመር ከፍተኛ ርብርብ በመደረግ ላይ መሆኑን ገልጸዋል።

በሰቆጣ፣ ላልይበላና ዋግኸምራ በጦርነቱ ተቋርጦ የቆየውን የኤሌክትሪክ ኃይል ዳግም ለማስጀመር ጥገና እየተደረገ ሲሆን ከአላማጣ ቆቦ እና ከአላማጣ ላልይበላ ያለው የኤሌክትሪክ ማስተላለፊያ መስመር ጥገና በአንድ ሳምንት ለማጠናቀቅ እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።

ከባህርዳር–አላማጣ የተዘረጋው የኃይል ማስተላለፊያ መሥመር እስኪጠገን ድረስም ከኮምቦልቻ–አላማጣ ያለውን ባለ 230 ኪሎ ቮልት መሥመር የመጠገን ሥራ በፍጥነት እየተከናወነ መሆኑ ተገልጿል።

በአሸባሪው ህወሓት የወደሙ የኤሌክትሪክ መሰረተ-ልማቶችን በመጠገን የኃይል አገልግሎቱን ለማስጀመር ከፍተኛ ርብርብ በመደረግ ላይ መሆኑንም ዳይሬክተሩ መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

በወልዲያ አላማጣ በኩል ያለው መስመር የጥገና ሥራ እየተከናወነ ሲሆን በወልቃይት ሑመራ እስከ ሽሬ ያለው መስመር ደግሞ የደረሰው ጉዳት መጠን ከታወቀ በኋላ የጥገና ሥራ እንደሚጀመር ገልጸዋል።