በአሸባሪው ሕወሓት የተጎዱ ዜጎችን መልሶ ለማቋቋም ሐብት እየተሰባሰበ ነው

ጥር 22/2014 (ዋልታ) በአሸባሪው ሕወሓት ወረራ ከመኖሪያቸው የተፈናቀሉና ንብረታቸው የወደመባቸውን ዜጎች መልሶ ለማቋቋም የሐብት ማሰባሰብ ሥራ እየተከናወነ መሆኑን የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትሯ ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) ገለጹ።
የሐብት ማሰባሰቡ በአገር ዐቀፍ ደረጃ በተቋቋመው በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሚመራውና ጉዳዩ በቀጥታ የሚመለከታቸው ሚኒስቴሮች እና ተጠሪ ተቋማት በተካተቱበት የአደጋ መከላከልና ዝግጁነት ብሔራዊ ኮሚቴ አማካኝነት እየተከናወነ ይገኛል።
የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ለመልሶ ማቋቋሙ የሃብት ማሰባሰብና ስርጭት ሥራውን በበላይነት እንደሚመራ ሚኒስትሯ ለኢዜአ ገልጸዋል።
በአማራና በአፋር ክልሎች ከቤት ንብረታቸው ለተፈናቀሉ ዜጎች የአስቸኳይ ጊዜ ሠብዓዊ እርዳታ እየተደረገ እንደሆነም ተናግረዋል።
በአማራ ክልል በጦርነቱና ተያያዥ ምክንያቶች ከ2 ነጥብ 3 ሚሊዮን በላይ፣ በአፋር ክልልም በጦርነትና በድርቅ አደጋ ከ1 ነጥብ 3 ሚሊዮን በላይ ዜጎች መፈናቀላቸውን ከተሰበሰቡ መረጃዎች ማረጋገጥ ተችሏል።
ተጎጂዎቹን ለማቋቋም ለ16 ቀናት በቆየውና “እኔ የእህቴ ጠባቂ ነኝ “በሚለው የሃብት ማሰባሰቢያ ንቅናቄ ከ2 ቢሊዮን ብር በላይ የሚገመት የምግብና የቁሳቁስ ድጋፍ መሰባሰቡንም ነው የገለጹት።
ከሴቶችና ወጣት አደረጃጀቶችም እንዲሁ ለመልሶ ማቋቋሙ ቀላል የማይባል ድጋፎች እየተደረጉ መሆኑን ሚኒስትሯ ገልጸዋል፡፡
ከተለያዩ ተቋማትም 93 ሚሊዮን 696 ሺሕ ብር የሚሆን የአይነት ድጋፍ መሰባሰቡን ተናግረዋል።
በሚኒስቴሩ እና በአማራ ክልል ባለው ተጠሪ ተቋሙ ጭምር በንቅናቄ በተከናወነ የሃብት ማሰባሰብ ሥራ በአጠቃላይ ከ2 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር በላይ የገንዘብና የአይነት ድጋፍ ማሰባሰብ ተችሏል ብለዋል።
ድጋፉን ለተረጂዎች ለማድረስ በቀጥታ የገንዘብ እንዲሁም የአይነት ድጋፍ የሚያገኙ የኅብረተሰብ ክፍሎች ልየታ መካሄዱንም ሚኒስትሯ ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) አብራርተዋል።
ልየታው ሴቶች፣ ሕጻናት፣ አረጋዊያንና አካል ጉዳተኞች በሚል መካሄዱን ጠቅሰው በአማራ ክልል 174 ሺሕ 603 ዜጎች የቀጥታ የገንዘብ ድጋፍ እየተሰጣቸው ነው ብለዋል።
የቀጥታ የገንዘብ ድጋፍ ተጠቃሚዎች የአይነት ድጋፍም የሚያገኙ ሲሆን በተጨማሪም ከ1 ነጥብ 3 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ዜጎችም እንዲሁ የአይነት ድጋፍ እያገኙ ነው ሲሉ አክለዋል።
በአጠቃላይ በክልሉ ከ1 ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ ተጎጂዎች ድጋፍ ማግኘታቸውን ሚኒስትሯ ተናግረዋል፡፡