መጋቢት 16/2014 (ዋልታ) በአሸባሪው ሸኔ ምክንያት በሰላም ወጥቶ መግባት አዳጋች እንደሆነባቸው ምዕራብ ሸዋ ዞን ነዋሪዎች ገለጹ፡፡
ብልፅግና ፓርቲ በምዕራብ ሸዋ ዞን እያደረገ በሚገኘው ሕዝባዊ ውይይት የዞኑ ነዋሪዎች ከመንግሥት አፋጣኝ ምላሽ የሚሹ ጥያቄዎችን አንስተዋል::
በዚህም የውይይቱ ተሳታፊዎች በምዕራብ ሸዋ ዞን እየተንቀሳቀሰ በሚገኘው የአሸባሪው ሸኔ ቡድን አማካይነት በአካባቢው የሚኖሩ ሕዝቦች አሰቃቂ ግድያና ዘረፋ እየደረሰባቸው መሆኑን ገልጸዋል፡፡
አካባቢው በሸኔ ቡድን መንቀሳቀሻ በመሆኑ ምክንያት በሰላም ወጥቶ መግባት አዳጋች እንደሆነ ያነሱት የውይይቱ ተሳታፊዎች መንግሥት ሰላምና ፀጥታ ለሚሻው የአካባቢው ነዋሪ ዘላቂ እና አፋጣኝ መፍትሄ እንዲሰጥ ጠይቀዋል::
በምዕራብ ሸዋ ዞንም በርካታ ተግባር ተኮር ሥራን የሚሹ የመሰረተ ልማት ዝርጋታ እንደሚያስፈልግም አንስተው በይበልጥም የመንገድ መሰረተ ልማት አለመሟላት የእለት ተእለት እንቅስቃሴያቸው ላይ እክል እንደፈጠረ ተናግረዋል::
እልባት ያጣው የዋጋ ንረት የማኅበረሰብን ኪስ ያላማከለ ከመሆኑ ባሻገር ህይወትን ለመግፋት አዳጋች እንደሆነባቸው የገለጹት ነዋሪዎች የምርት እጥረት ሳይኖር በዋናነት ለዋጋ ንረት የአንበሳውን ሚና እየተጫወቱ የሚገኙ ስግብግብ ነጋዴዎች ላይ እርምጃ እንዲወሰድባቸውም ጠይቀዋል::
በውይይት መድረኩ የትራንስፖርት ሚኒስትር ዴኤታ ካሳሁን ጎፌ፣ የአምቦ ከተማ ከንቲባ ሃጫሉ ገመቹ፣ አባገዳዎች፣ ሀደ ሲንቄዎች እንዲሁም ሌሎች የማኅበረሰብ ክፍሎች ተገኝተዋል፡፡
ሔብሮን ዋልታው (ከአምቦ)
ለፈጣን መረጃዎች፦
ፌስቡክ https://bit.ly/3Ma7QTW