በአሸባሪው ቡድን ከወደሙ የጤና ተቋማት እስካሁን 64 የሚሆኑ አገልግሎት መስጠት መጀመራቸው ተገለጸ

የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ

ታኅሣሥ 14/2014 (ዋልታ) በአፋር እና በአማራ ክልሎች የወደሙ የጤና ተቋማትን መልሶ ሥራ ለማስጀመር በተደረገ እንቅስቃሴ እስካሁን 64 የሚሆኑ የጤና ተቋማት በድጋሚ አገልግሎት እንዲሰጡ ማድረግ መቻሉን የጤና ሚኒስቴር አስታወቀ።

የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ የጤና ተቋማትን መልሶ ለማቋቋም እየተከናወኑ ያሉ ተግባራትን በተመለከተ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ የአሸባሪውና ወራሪው ሕወሓት ቡድን ወረራ ባካሄዳቸው በአማራ እና አፋር ክልሎች የወደሙ የጤና ተቋማትን መልሶ ለማደራጀት እና ወደ ሥራ ለማስገባት ከፍተኛ እንቅስቃሴ እየተደረገ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

የሽብር ቡድኑ በፈፀመው ወረራ የህክምና ተቋማትን ከማውደም ባለፈ የህክምና መሳሪያዎችን እና መድኃኒቶችን እንደዘረፈም ተናግረዋል።

በሁለቱ ክልሎች የወደሙ የጤና ተቋማትን መልሶ ሥራ ለማስጀመር እና ለማደራጀት በተለያዩ መንገዶች የሀብት ማሰባሰብ ሥራ እየተከናወነ እንደሚገኝም ጠቁመዋል።

በተጨማሪም ጦርነቱ በጤና ዘርፍ ላይ የሚያደርሰውን ተፅዕኖ ለመቀነስ የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ እንደሚገኙ ተነግሯል።

በሌላ ዜና የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ሥርጭት በከፍተኛ ሁኔታ በመሰራጨት ላይ እንደሚገኝ የገለጹት ሚኒስትሯ ኅብረተሰቡ ለኮቪድ 19 ወረርሽኝን የመከላከያ እና የመቆጣጠሪያ  መንገዶችን መተግበሩ ላይ ከፍተኛ መዘናጋት እያሳየ ነእንደሆነም አመልክተዋል፡፡

በመሰረት ተስፋዬ