በአትሚስ የሚገኘው የኢትዮጵያ 7ኛ ሞተራይዝድ ሻለቃ የሠራዊት አባላት የመከላከያ ቀንን አከበሩ

ጥቅምት 16/2015 (ዋልታ) “የጥንካሬያችን ምንጭ ሕዝባችን ነው” በሚል መሪ ቃል የመከላከያ ሠራዊት ቀንን በአትሚስ የሚገኘው የኢትዮጵያ 7ኛ ሞተራይዝድ ሻለቃ የሠራዊት አባላት በፓናል ውይይት አከበሩ።

የ7ኛ ሞተራይዝድ ሻለቃ ዋና አዛዥ ኮ/ል ወዳጅ ቦጋለ በፓናል ውይይቱ ላይ ተገኝተው እንደተናገሩት ኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ የራሷን ሠራዊት በሚኒስቴር መስሪያ ቤት ያቋቋመችበትን ቀን ጥቅምት 15/1900 ዓ.ም የሠራዊት ቀን ሆኖ መከበሩ ለሠራዊቱ ከፍተኛ አስተዋፆ አለው።

የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት በሁሉም አካባቢ እና ቀጠና የተሰጠውን ግዳጅ በአመርቂ ድል ሲፈፅም ጠንካራው ህዝባችን ከጎናችን አልተለየም ይህንንም በዓል ስናከበር ህዝባችንንም እያወደስን እና እያመሰገንን መሆን አለበት ሲሉ ተናግረዋል።

ከፍተኛ መኮንኑ አክለውም የአለም መንግስታት በሶማሊያ የሰጡንን ትልቅ ኃላፊነት እና አደራ በብቃት እና በጥራት በመወጣት ላይ እንገኛለን ይህንንም ተግባር አጠናክረን ለመቀጠል ይህ በዓል ከፍተኛ አበርክቶ አለው ብለዋል።

በፓናል ውይይቱ ላይ ተሳታፊ ከነበሩት የሠራዊት አባላት መካከል ሻ/ል ዘመኑ አበራ እና አስር አለቃ ደመላሽ ጌትነት በሰጡት አስተያዬት የመከላከያ ሠራዊት ቀንን በአትሚስ ተልዕኮ ላይ ሆነን ስናከብር ለምንፈፅመው ግዳጅ ትልቅ አስተዋፆ አለው ማለታቸውን የመከላከያ ሰራዊት መረጃ አመልክቷል።