በ‘አንድ ሚሊዮን ወደ የአገር ቤት’ ጥሪ የጤና ቁሳቁስ ድጋፍ ማድረግ የሚያስችል ዘመቻ ተጀመረ

ታኅሣሥ 8/2014 (ዋልታ) በ‘አንድ ሚሊዮን ወደ የአገር ቤት’ ጥሪ የጤና ቁሳቁስ ድጋፍ ማድረግ የሚያስችል ዘመቻ ተጀመረ።
‘አንድ ሻንጣ ለወገኔ’ በሚል መሪ ሀሳብ የተጀመረው እንቅስቃሴ ወደ ኢትዮጵያ የሚመጡ ዳያስፖራዎች የመድኃኒት ድጋፍ ይዘው እንዲመጡ የማድረግ ዓላማ ያለው መሆኑ ተገልጿል፡፡
አሸባሪው ሕወሓት በአማራና አፋር ክልሎች በፈጸመው ወረራ በሺሕዎች በሚቆጠሩ የጤና ተቋማት ላይ በፈጸመው ውድመትና ዝርፊያ ምክንያት ዜጎችና ተቋማት ለችግር መጋለጣቸው ይታወቃል።
በርካታ ዜጎች የጤና አገልግሎት የሚያገኙባቸው የሕክምና ቁሳቁስ ስለሚያስፈልጋቸው ወደ አገር ቤት የሚመጡ ዳያስፖራዎችም የሕክምና ግብአቶችን ይዘው እንዲመጡ ጥሪ ቀርቧል።
መድኃኒቶች፣ የሕክምና መሳሪያዎችና ሌሎች የጤና መገልገያ እቃዎችን ይዘው በመምጣት የጤና ቁሳቁስ ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው ወገኖችና የጤና ተቋማት እንዲደርሱ ተጠይቋል።
ወደ አገር ቤት መምጣት የማይችሉ ዳያስፖራዎች ድጋፋቸውን በሌላ ሰው በማስላክ እንዲደግፉ የዘመቻው አስተባባሪዎች ለኢዜአ ገልጸዋል።
ዳያስፖራው የሚያመጣውን የጤና ቁሳቁስ ድጋፍ በቦሌ ዓለም ዐቀፍ አየር ማረፊያ በማሰባሰብ ድጋፉ ለሚያስፈልጋቸው ወገኖች እንደሚከፋፈልም አመልክተዋል።