ታኅሣሥ 27/2015 (ዋልታ) በአንድ ሳምንት ጊዜ ውስጥ ብቻ ከ360 ሺሕ ሊትር በላይ ነዳጅ ወደ ትግራይ ክልል መጓጓዙን የኢትዮጵያ ነዳጅና ኢነርጂ ባለሥልጣን አስታወቀ።
የባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ሰሃረላ አብዱላሂ መንግሥት ግብረ-ኃይል በማቋቋም ነዳጅ ያለምንም መስተጓጎል ከጂቡቲ ወደ ክልሉ በቀጥታ እንዲገባ እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ባለስልጣኑ ከታኅሣሥ 19 ቀን 2015 ዓ.ም ጀምሮ ወደ ክልሉ ነዳጅ እንዲጓጓዝ ለነዳጅ አቅራቢዎች ፈቃድ መስጠቱን ያስታወሱት ኃላፊዋ ይህን ተከትሎም ባለፈው አንድ ሳምንት በስምንት የነዳጅ ማመላለሻ ተሽከርካሪዎች ከ360 ሺሕ ሊትር በላይ ነዳጅ ወደ ትግራይ ክልል መጓጓዙን ተናግረዋል፡፡
በተለይ በመቀሌ የሚገኙ የነዳጅ ማደያዎች በጦርነቱ ጉዳት ያልደረሰባቸው በመሆኑ ከማደያዎቹ ባለቤቶችና ኩባንያዎች ጋር በመነጋገር ሙሉ በሙሉ ወደ ሥራ እንዲገቡ ማድረግ መቻሉንም ገልጸዋል።
በተጨማሪም የነዳጅ አቅርቦቱ በሁሉም የክልሉ ከተሞች እንዲዳረስ እየተሠራ መሆኑን መጥቀሳቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
በአጠቃላይ መንግስት እያከናወነው ያለው ሥራ የነዳጅ አቅርቦቱን ተደራሽ በማድረግ ረገድ ተጨማሪ አቅም የሚፈጥር መሆኑንም አብራርተዋል፡፡
እስካሁን ባለው ሂደትም ከመቀሌ እስከ ዛልአንበሳ ያሉ ቶታል፣ ኖክ፣ ታፍና ኦይል ሊቢያ ማደያዎች የነዳጅ ጭነት ትዕዛዝ ማስተላለፋቸውን ጠቅሰዋል፡፡
በክልሉ ለሁለት ዓመታት ያህል የነዳጅ ማደያዎች ተዘግተው የቆዩ በመሆኑ ”እንዲያውቁት” በሚል አሁን ያለውን ሀገራዊ የነዳጅ የመሸጫ ዋጋ ዝርዝር መላኩንም ጠቁመዋል።