ሰኔ 10/2014 (ዋልታ) በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጉለሌ ክፍለ ከተማ በአንድ ተማሪ ላይ የድብደባ ወንጀል ፈጽመዋል የተባሉ የፖሊስ አባላትን በቁጥጥር ስር አውሎ ምርመራ እያደረገ መሆኑን የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታወቀ፡፡
የፖሊስ አባላት የህግ በላይነትን ለማስጠበቅ በሚያከናውኑት የትኛውም ዓይነት እንቅስቃሴ የሰው ልጆች ሰብዓዊ መብቶችን አክብሮ በማስከበር ህጋዊ አግባብ መሆን እንዳለበት የአዲስ አበባ ፖሊስ ጉዳዩን አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ አስገንዝቧል፡፡
በጉለሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 7 ሰሜን ማዘጋጃ ጋበር ሆቴል በሚባል አካባቢ ሰኔ 8 ቀን 2014 ዓ.ም ከቀኑ 5 ሰዓት ላይ በክፍል ውስጥ ርቺት ተኩሶ ከትምህርት ቤት ውስጥ አምልጦ የሄደ አንድ ተማሪ አራት የፖሊስ አባላት ተከታትለው በመያዝ የድብደባ ወንጀል እንደፈጸሙበት በመግለጫው ተመላክቷል፡፡
ህገ- ወጥ ድርጊቱ በማህበራዊ ሚዲያ ከተለቀቀ በኋላ ፖሊስ ባደረገው ማጣራት ድል በር 2ኛ ደረጃ በሚባል ትምህር ቤት ‘የ12ኛ ክፍል ማጠናቀቂያ ነው’ በሚል ፕሮግራም ላይ በክፍል ውስጥ በተደረገ ዝግጅት አንድ ተማሪ ርችት እንደተኮስ እና በትምህርት ቤት ውስጥ ርችት መተኮሱ ሌሎች ተማሪዎችን እንደረበሻቸው ለፖሊስ መረጃ መድረሱ ተጠቁሟል፡፡
በዕለቱ ድርጊቱን ፈፅሟል የተባለው ተማሪ ከትምህርት ቤቱ ቅጥር ግቢ እንደወጣ የተነገራቸው አራት የጉለሌ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ አባላት ክትትል በማድረግ ሰሜን ማዘጋጃ ጋበር የሚባል ሆቴል አካባቢ ተማሪውን ይዘውት ተገቢ ያልሆነ ድብደባ መፈጸማቸውም ተገልጿል፡፡
የአዲስ አበባ ፖሊስ መረጃው ካደረሰው በኋላም ተጠርጣሪ የፖሊስ አባላቱን በቁጥጥር ስር አውሎ ምርመራ እያደረገ እንደሚገኝ አስታውቋል፡፡
በማንኛውም ሁኔታ ውስጥ የህግ አስከባሪነት መነሻው ህግን ማክበር መሆኑን የገለጸው የከተማዋ ፖሊስ የዜጎችን ህጋዊ መብት በሚፃረሩ የፖሊስ አባላት ላይ የሚወስደውን ዕርምጃ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስገንዝቧል፡፡
በማንኛውም ሁኔታ ህገወጥ ተግባር ሲፈጸም ህብረተሰቡ በያገባኛል ስሜት የሚሰጠውን መረጃ አጠናክሮ እንዲቀጥልም ጥሪ ማቅረቡን ከአዲስ አበባ ፖሊስ ያገኘነው መረጃ አመላክቷል፡፡