በአዋጁ ትግበራ በተደረገ ክትትል 237 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ዋሉ

ጥቅምት 30/2014 (ዋልታ) በደቡብ ክልል በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ትግበራ ከጸጥታ ኃይሉ ጋር በተደረገ ጥብቅ ክትትል 237 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ።

የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ነብዩ ኢሣያስ አሸባሪው ሕወሓትና ሸኔ ሀገር በማፍረስ ሴራ መጠመዳቸውን ጠቅሰው ቡድኖቹን ለመመከት ከማህበረሰቡ ጋር በመቀናጀት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

የፀጥታ አካላት ጭምር በተጠርጣሪነት በቁጥጥር ስር መዋላቸው ያነሱት ኮሚሽነሩ እነዚህ ተጠርጣሪዎች የሽብር ቡድኑን በገንዘብ፣ በሞራል፣ በሀሳብና መረጃ በማቀበል ሲረዱ የነበሩ ናቸው ብለዋል፡፡

46 የጦር መሳሪዎች መያዛቸውን ገልጸው አካል ጉዳተኛ በመምሰል የሽብር ቡድኑን ዕኩይ ተልዕኮ የያዙ ግለሰቦችም በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ተናግረዋል።

ማንኛውም ግለሰብ ማንነቱን የሚገልፅ መታወቂያ መያዝ እንዳለበት እና የጦር መሳሪያ ያለው ግለሰብም ማስመዝገብ እንዳለበት ማሳሰባቸውን ከክልሉ ኮዩሙኒኬሽን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡