በአውሮፓ ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ለተፈናቀሉ ወገኖች ከ73 ሺሕ ዩሮ በላይ ገንዘብ ተሰበሰበ

ጥቅምት 14/2015 (ዋልታ) በጣልያን፣ ግሪክና ማልታ ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በአሸባሪው ሕወሓት ወረራ ምክንያት ለተፈናቀሉ ዜጎች የሚውል ከ73 ሺሕ ዩሮ በላይ ገንዘብ መሰብሰቡ ተገለጸ።

“የእናት አገር ጥሪ” በሚል መሪ ሀሳብ የበይነ መረብ የገቢ ማሰባሰቢያ ቴሌቶን ትናንት ተካሄዷል።

መርሐግብሩን ያዘጋጁት የሮም የእርዳታ አሰባሳቢ ኮሚቴ፣ በጣሊያን የዲፌንድ ኢትዮጵያ አስተባባሪዎችና በጣልያን የኢትዮጵያ ኤምባሲ በጋራ በመተባበር ነው።

በዝግጅቱ በጣልያን፣ ግሪክና ማልታ ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትወልደ-ኢትዮጵያውያውን ከ73 ሺሕ ዩሮ በላይ የገንዘብ ድጋፍ መሰብሰቡን በጣልያን የኢትዮጵያ ኤምባሲ አስታውቋል።

ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያኑ በየአካባቢያቸው በጋራ እና በተናጠል ሆነው ጨረታዎችን የመሳተፉ ሲሆን ቀጥታ ድጋፎችን ማድረጋቸውም ገልጿል።

በጣልያን የኢትዮጵያ አምባሳደር ደሚቱ ሐምቢሳ ዳያስፖራው አገር ስትጣራ ሁሌም አለን በማለት ለሚያደርገው ሁሉን አቀፍ ድጋፍ ምስጋናቸውን አቅርበው ድጋፉን አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል።

አርቲስት ስለሺ ደምሴ (ጋሽ አበራ ሞላ) በበኩሉ ለኢትዮጵያ ምንም አይነት የምንቆጥበው ጉልበትም ሆነ ገንዘብ የለም፤ በጋራ ከቆምን ችግሮቻችንን እንሻገራለን ብሏል።

ትልቅነት አንድ ከመሆን ብቻ የሚገኝ እንደሆነም ገልጿል።

ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵውያን በዘርፈ ብዙ ጫናዎች እያለፈች ለምትገኘው አገራቸው ለምትፈልገው ድጋፍ ምላሽ መስጠታቸውን እንደሚቀጥሉ መናገራቸውን ኤምባሲው በመግለጫው አመልክቷል።