በአውስትራሊያ በኢትዮጵያ ላይ ጫና ለማድረግ የሚሞክሩ ሀይሎችን የሚያወግዝ ሰልፍ ተካሄደ

መጋቢት 10/2013 (ዋልታ) – በአውስትራሊያ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን፣ ትውልደ ኢትዮጵያውያንና የኢትዮጵያ ወዳጆች የኢትዮጵያ መንግስት የወሰደውን የህግ ማስከበር ዘመቻ በመደገፍና የዓለም አቀፉን ማህበረሰብ በማደናገር በኢትዮጵያ ላይ ህጋዊ ያልሆነ ጫና ለማድረግ የሚሞክሩ ሀይሎችን በማውገዝ በካንቤራ ከተማ ሰላማዊ ሰልፍ አካሄዱ።

ሰልፈኞቹ መንግስት በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል ህግ ለማስከበር የወሰደውን እርምጃ እንደሚደግፉ፣ የሃሰት መረጃ በማሰራጨት ዓለም አቀፉን ማህበረሰብ ለማሳሳት የሚሰሩ አካላትን እንደሚቃወሙ ገልጸዋል፡፡

እንዲሁም ምዕራባውያን ሃገራት ኢትዮጵያ ሉዓላዊነቷን ለማስጠበቅና አንድነቷን ለማስቀጠል የምትወስደውን እርምጃ ከመደገፍ ባሻገር በውስጥ ጉዳይዋ ጣልቃ መግባት የሌለባቸው መሆኑን የሚያሳዩ መፈክሮችን ያሰሙ ሲሆን፣ በኢትዮጵያውያን መካከል ትብብርና ወንድማማችነትን የሚያጠናክሩ መልዕክት ማስተላለፋቸውን ከዳያስፖራ ኤጀንሲ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡