በአውስትራሊያ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን የድጋፍ ሰልፍ አካሄዱ

መጋቢት 03/2013 (ዋልታ) – በአውስትራሊያ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን፣ ትውልደ ኢትዮጵያውያንና የኢትዮጵያ ወዳጆች በኢትዮጵያ ያለውን ትክክለኛ ሁኔታ ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ለማሳወቅና በኢትዮጵያ ላይ እየተፈጸሙ ያሉ ተገቢ ያልሆኑ ጫናዎችን ለመቃወም የድጋፍ ሰልፍ አካሂደዋል።
ሰልፈኞቹ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት እንዲያከብርና በኢትዮጵያ ላይ ሆን ተብሎ እየተነዙ ባሉ የተሳሳቱ መረጃዎች ሰለባ ከመሆን ራሱን እንዲጠብቅ ድምጻቸውን አሰምተዋል።
እንዲሁም ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች ዘገባቸውን በሚዛናዊነት እንዲሰሩ የጠየቁ ሲሆን፣ የሱዳን መንግስት በኢትዮጵያ ላይ የፈጸመውን ወረራም አጥብቀው እንደሚያወግዙ መግለፃቸውን ከኢትዮጵያ ዲያስፖራ ኤጀንሲ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡