በአዲሱ የኮሮናቫይረስ ዝርያ ምክንያት አገራት ጥብቅ እርምጃ እየወሰዱ ነው

አዲሱ የኮሮናቫይረስ ዝርያ

በዩናይትድ ኪንግደም የተገኘው አዲሱ የኮሮናቫይረስ አይነት መላው ዓለምን አስግቷል።

አገራት ወደ ዩናይትድ ኪንግደም የሚደረግ በረራን አግደዋል። በዚህም ከ40 በላይ አገራት ከዩናይትድ ኪንግደም ወደ አገራቸው የሚደረጉ በረራዎችን ማገዳቸው ተገለጸ።

የአውሮፓ ሕብረት አባል አገራትም በዚህ ዙሪያ የጋራ ፖሊሲ ለማውጣት እየተወያዩ ነው።

ዴንማርክ ውስጥ አዲሱ የቫይረስ ዝርያ በመታየቱ ስዊድን ወደ ዴንማርክ የሚደረግ ጉዞ አግዳለችም የተባለው።

ዝርያው በከፍተኛ ሁኔታ የሚሰራጭ ነው። በከፍተኛ ደረጃ ጎጂ ስለመሆኑ ግን እስካሁን የተገኘ መረጃ የለም።

የዓለም ጤና ድርጅቱ ማይክ ራየን እንደሚሉት፤ አዲሱ የቫይረስ ዝርያ በወረርሽኙ ዝግመተ ለውጥ ሂደት የሚጠበቅ ነው።

የዩናይትድ ኪንግደም የጤና ሚኒስትር ጸሐፊ ማት ሀንኮክ ከሰጡት ማብራሪያ በተቃራኒው አዲሱ ዝርያ “ከቁጥጥር አልወጣም” ብለዋል።

ዩናይትድ ኪንግደም ከተገኘው የቫይረስ ዝርያ የተለየ አዲስ ዝርያ በደቡብ አፍሪካም ተገኝቷል። በዚህም የደቡብ አፍሪካ ተጓዦች ላይ እገዳ እየተጣለ ነው ሲል ቢቢሲ ዘግቧል።