በአዲስ አበባና በኦሮሚያ ዙሪያ ገበያን ለማረጋጋት የጋራ ግብረ-ኃይል ተቋቋመ

ነሃሴ 21/2013 (ዋልታ) – በአዲስ አበባና በኦሮሚያ ዙሪያ የኢኮኖሚ አሻጥር እና ህገ-ወጥነትን በመግታት ገበያን ለማረጋጋት ለማስቻል የጋራ ግብረ-ኃይል ተቋቁሟል፡፡

የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ ኃላፊ አቶ አብዱልፈታ የሱፍ  ቀደም ሲል ከጁንታው ጋር ትስስር የነበራቸው እና ጥቅማቸው የተነካ አንዳንድ ነጋዴዎች በከተማዋ ምርትን በህገ-ወጥ መንገድ ማከማቸትና መደበቅ፣ ኢኮኖሚያዊ ምክንያት የሌለው የምርቶች እና አገልግሎቶች የዋጋ ንረት መፍጠር  የኑሮ ውድነትና የገበያ አለመረጋጋት እንዲፈጠር እያደረጉ ይገኛሉ ብለዋል፡፡

ከችግሩ ግዝፈት አንፃር የኢኮኖሚ አሻጥርና የንግድ ህገ-ወጥነት የሚፈጽሙ አካላት ተግባራቸውም ሆነ ተጽዕኗቸው ሀገር አቀፍ ሊሆን ስለሚችል ተገቢውን እርምጃ በወቅቱ ለመውሰድ እንዲቻል  የአዲስ አበባ እና የኦሮሚያ የንግድ ቢሮዎች የጋራ ግብረ-ኃይል በማዋቀር ስራውን መምራት  ማስፈለጉን ተናግረዋል፡፡

የኦሮሚያ ብሔራዊ  ክልል ንግድ ቢሮ ኃላፊ አቶ ደንጌ ቦሩ  በበኩላቸው ሀገሪቱ አሁን ያለችበትን ሁኔታ  ከግምት ውስጥ በማስገባት በአንድነትና በጋራ መቆም እንደሚገባ አውስተዋል።

በኦሮሚያ በኩልም በአጎራባች ከተሞችና አካባቢዎች ያሉ ፋብሪካ ባለቤቶች ምርታቸውን ወደ አዲስ አበባ በማጓጓዝ አዲስ አበባ የሚደብቁበት ሁኔታ ስላለ የጋራ ግብረ-ኃይል ስምሪቱ በዚህ ላይ ትከረት አድርጎ እንደሚሰራም ጠቁመዋል።

በዋናነትም የማከማቻ መጋዘኖች ፍተሻ፣ ምርት አቅርቦት፣ ህግ ማስከበርና እና ደረሰኝ ግብይት ላይ አተኩረን እንሰራለን ያሉት ሃላፊው የተለያዩ ትስስሮችን በመፍጠር አብሮ ለመስራት ዝግጁ መሆናቸውን መናገራቸውን  ከአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡