የሕዳሴው ግድብ ዋንጫ በመዲናዋ በተዘዋወረባቸው ሰባት ወራት 2 ቢሊዮን ብር ድጋፍ መሰብሰቡን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አስታወቀ።
ዋንጫው በከተማዋ የነበረው ቆይታ ተጠናቆ ወደ ተረኞቹ ሐረሪ ክልልና ድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ሽኝት ተደርጎለታል።
ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ በጥናት የተጀመረ እንደመሆኑ ግንባታው ሳይጠናቀቅ እንደማይቆም በሽኝት መርሃ ግብሩ ላይ ተናግረዋል።
“የሕዳሴው ግድብ የብልፅግና ጉዟችንን የሚያፋጥን በሕዳሴ ምዕራፍ ውስጥ የሚደምቅ የአገራችንና የከተማችን ብርሃን ነው” ሲሉ ተናግረዋል።
የከተማ አስተዳደሩ የግድቡ ግንባታ ከተጀመረበት ጊዜ አንሰቶ እስካሁን ከ3 ቢሊዮን ብር በላይ ድጋፍ ማድረጉን ያስታወሱት ምክትል ከንቲባዋ፣ ባለፉት ሰባት ወራት ብቻ ከ2 ቢሊዮን ብር መሰብሰቡን ገልፀዋል።
ምክትል ከንቲባዋ ለግድቡ ግንባታ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ያደረጉ አካላትንም አመስግነዋል።
የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ሕዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ብሔራዊ ምክር ቤት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አረጋዊ በርሄ የሕዳሴ ዋንጫ “ግድቡ በህብረተሰቡ ወስጥ የዕለት ተዕለት አጀንዳ እንዲሆን በማድረግ በርካቶች የራሳቸውን አሻራ እንዲያስቀምጡ ያደረገ ነው” ብለዋል።
በግድቡ ግንባታ አሻራቸውን ያኖሩ አካላትን አመስግነው ግንባታው እስከሚጠናቀቅ ድጋፋቸውን እንዲያጠናክሩ ጥሪ አቅርበዋል።
በዋንጫው ሽኝት መርሃ ግብር ለግድቡ ግንባታ አስተዋፅኦ ላደረጉ ባለሀብቶችና ተቋማት የምስጋናና የእውቅና ሽልማት መበርከቱን ከአዲስ አበባ ፕሬስ ሴከሬተሪ ጽ/ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።