በአዲስ አበባ በቀን 75 ሺሕ ሜትሪክ ኪዩብ ውኃ የሚያመርት ፕሮጀክት ወደ ሥራ ለማስገባት እየተሰራ ነው

ሰርካለም ጌታቸው

የካቲት 17/2015 (ዋልታ) በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በቀን 75 ሺሕ ሜትሪክ ኩዩብ የሚያመርት የውኃ ልማት ፕሮጀክት ወደ ሥራ ለማስገባት እየተሰራ መሆኑን የከተማ አስተዳደሩ ውሃና ፍሳሽ ባለሥልጣን ገለጸ።

የባለሥልጣኑ የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ሰርካለም ጌታቸው በመዲናዋ የውሃ ፍላጎትና አቅርቦትን ለማጣጣም እየተሰራ መሆኑን ገልጸው ለዚህም ከገጸ ምድርና ከርሰ ምድር ውሃ አጣርቶ በማምረት ለኅብረተሰቡ ተደራሽ እያደረገ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡

ከገጸ ምድር የሚገኘው ውኃ ከለገዳዲ፣ ገፈርሳና ከድሬ ግድብ መሆኑን አብራርተው ከከርሰ ምድር ደግሞ ከ220 በላይ ከሚሆኑ ጉድጓዶች ውሃ እየተመረተ መሆኑን ገልጸዋል።

አሁን ላይ በአዲስ አበባ ከተማ ያለው የውኃ ፍላጎት 1 ነጥብ 2 ሚሊየን ሜትሪክ ኪዩብ ሲሆን በአንጻሩ ከተማዋ ለነዋሪዎቿ ማቅረብ የምትችለው 725 ሺሕ ሜትሪክ ኪዩብ ውሃ ነው ብለዋል።

በመዲናዋ የሪል ስቴቶች፣ ትምህርት ቤቶች፣ ሆቴሎችና ፋብሪካዎች መስፋፋት ለውሃ ፍላጎቱ መጨመርና ከአቅርቦት ጋር እንዳይጣጣም አድርጓል ነው ያሉት።

ይህንንም ተከትሎ ከ1 ሺሕ 50 በላይ ቦታዎች ላይ በፈረቃ እንደሚሰራ ገልጸው ይህንን የውኃ ፍላጎት ለማጣጣም በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ነው ያመላከቱት።

ባለሥልጣኑ ተደራሽነት ላይ ያሉ ክፍተቶችን ለመሙላት የውሃ ኔትዎርክ ላይ ከፍተኛ ሥራዎችን እየሰራ እንደሚገኝ ማንሳታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡