በአዲስ አበባ ቦሌ ክፍለ ከተማ ትናንት ምሽት በደረሰ የእሳት አደጋ 3 ሚሊዮን ብር ግምት ያለው ንብረት ወደመ

መጋቢት 23/2013 (ዋልታ) በአዲስ አበባ ቦሌ ክፍለ ከተማ ትናንት ማምሻውን በደረሰ የእሳት አደጋ 3 ሚሊዮን ብር የሚገመት ንብረት መውደሙን የከተማዋ የእሳትና የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን አስታወቀ።

የኮሚሽኑ የሕዝብ ግንኙነት ቡድን መሪ አቶ ጉልላት ጌታነህ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ገርጂ መብራት ኃይል አካባቢ ትናንት ምሽት አንድ ሰአት ገደማ ላይ የተነሳ የእሳት አደጋ በ12 መኖሪያ ቤቶች ላይ ጉዳት አድርሷል።

በአደጋው ከወደመው ንብረት በተጨማሪ የመቁሰል አደጋ የደረሰባቸው አምስት ሰዎች የሕክምና ክትትል እየተደረገላቸው መሆኑን አቶ ጉልላት ገልጸዋል።

አደጋውን ለመቆጣጠር 45 ደቂቃ የፈጀ ሲሆን፣ 36 የአደጋ ጊዜ ሰራተኞች፣ አምስት የድንገተኛ አደጋ ተሽከርካሪዎችና ሁለት አምቡላንሶች እሳቱን ለማጥፋት ተሰማርተው እንደነበር ተናግረዋል።

“እሳቱን ለመቆጣጠር 30 ሺህ ሊትር ውሃ ጥቅም ላይ ውሏል” ብለዋል።

የእሳት አደጋ ሰራተኞች፣ ፖሊስና የአካባቢው ማህበረሰብ ባደረገው ርብርብ 12 ሚሊዮን ብር የሚገመት ንብረት ከውድመት መዳኑንም አቶ ጉልላት ተናግረዋል።

የአካባቢው ማህበረሰብ የእሳት አደጋውን ለመቆጣጠር ላደረገው ትብብር አመስግነው፤ የአደጋው መንስኤ ሲጣራ ውጤቱ ለሕብረተሰቡ ይፋ እንደሚደረግ ገልጸዋል።

በቀጣይም ሕብረተሰቡ የእሳትና ድንገተኛ አደጋ እንዳይከሰት አስፈላጊውን ሁሉ ጥንቃቄ እንዲያደርግ አሳስበዋል።

የእሳትና ድንገተኛ አደጋ ሲያጋጥም በነጻ የስልክ መስመር 939፤ በቀጥታ የስልክ መስመሮች 011 155 53 00 ወይም በ011 156 86 01 ደውሎ ማሳወቅ እንደሚችል ይፋ አድርገዋል።