ሰኔ 25/2013 (ዋልታ) – በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ከሰኔ 23 እስከ 25 ቀን 2013 ዓ.ም ድረስ ሲሰጥ የቆየው የ8ኛ ክፍል ክልላዊ ፈተና በሰላም ተጠናቋል፡፡
የከተማ አስተዳደሩ ትምህርት ቢሮ ሃላፊ አቶ ዘላለም ሙላቱ የ8ኛ ክፍል ክልላዊ ፈተና በሁሉም የመፈተኛ ጣቢያዎች ተማሪዎች ፈተናውን ያለምንም የፀጥታ ችግር በተረጋጋ ሁኔታ መውሰዳቸውን ገልጸዋል፡፡
በቢሮው የፈተና ዝግጅትና አስተዳደር ዳይሬክተር አቶ ዲናኦል ጫላ በመዲናዋ ለሶስት ተከታታይ ቀናት በ175 የመፈተኛ ጣቢያዎች 72 ሺህ 694 ተማሪዎች ፈተና መውሰዳቸውን ተናግረዋል፡፡
በአንጻሩ ከ1 ሺህ 80 በላይ ተማሪዎች ክልላዊ ፈተናውን አለመውሰዳቸውን ጠቁመዋል፡፡
ለፈተናው በሰላም መጠናቀቅ በከተማ እና በየደረጃው የተደራጀው ኮማንድ ፖስት፣ የፀጥታ አካላት፣ መምህራን፣ የትምህርት ባለሙያዎች፣ ወላጆች፣ ተማሪዎች እና ሁሉም የትምህርት ባለድርሻ አካላት ለነበራቸው አስተዋጽኦ የቢሮ ሃላፊው አቶ ዘላለም ምስጋና ማቅረባቸውን ከአስተዳደሩ ትምህርት ቢሮው ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡