ነሃሴ 06/2013 (ዋልታ) -የአዲስ አበባ ከተማ ገቢዎች ቢሮ ከሀምሌ 01 እስከ ሀምሌ 30/2013 ዓ.ም በሶስቱም ደረጃ ግብር ከፋዮች 5 ቢሊዮን 820 ሚሊየን 260 ሺህ ብር መስብሰቡን አስታወቀ።
ቢሮው በተጠቀሰው ጊዜ 5 ቢሊዮን 390 ሚሊዮን 930 ሺህ ብር ለመሰብሰብ አቅዶ የነበረ ሲሆን፤ 5 ቢሊዮን 820 ሚሊየን 260 ሺህ ብር በመሰብሰብ የእቅዱን 108 በመቶ መሰብሰቡን ገልፀዋል።
ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር 1 ቢሊዮን 126 ሚሊዮን 950 ሺህ ብር ወይም 24 በመቶ ብልጫ እንዳለው የገቢዎች ቢሮ ኃላፊ ሙሉጌታ ተፈራ ገልጸዋል ።
ከሀምሌ 1/2013 እስከ ጥቅምት 30/2014 ዓ.ም ድረስ ዋነኛ የግብር ማሳወቂያና መክፈያ ወቅቶች ናቸው ያሉት አቶ ሙሉጌታ በተለይም ወርሃ ሐምሌ ደግሞ የደረጃ “ሀ እና ለ” ግብር ከፋዮች እንደተጠበቀ ሆኖ የደረጃ “ሐ” ግብር ከፋዮች ግብሮቻቸውን የሚከፍሉበት ብቸኛ ወር መሆኑም አመልክተዋል።
በተጠናቀቀው የ2013 በጀት ዓመት በከተማዋ 42 ቢሊዮን 606 ሚሊዮን ብር ገቢ መሰብሰብ መቻሉን የገለፁት የቢሮ ኃላፊው አፈፃፀሙም ባለፉት 8 ዓመታት ከተሰበሰው ገቢ የላቀ መሆኑንም ከከተማው ፕሬስ ሴክሬታሪያት የተገኘው መረጃ ያመለክታል።