በአዲስ አበባ የተባበሩት አረብ ኢሚሬትስ ኤምባሲ ላይ የሽብር ጥቃት ለመፈፀም ሲንቀሳቀሱ የነበሩ የሽብር ቡድን አባላት በቁጥጥር ስር ዋሉ

ከውጭ የሽብር ቡድን አባላት ተልእኮ በመቀበል አዲስ አበባ በሚገኘው የተባበሩት አረብ ኢሚሬትስ ኤምባሲ ላይ የሽብር ጥቃት በመፈጸም በሰው ሕይወት እና በንብረት ላይ ከፍተኛ ጉዳት ለማድረስ እንዲሁም የአፍሪካና የዓለም አቀፍ የዲፕሎማሲ ተቋማት መቀመጫ የሆነችውን የአዲስ አበባን በጎ ገጽታ ለማበላሸት በዝግጅት ላይ እንዳሉ የብሔራዊ መረጃ ደህንነት አገልግሎት ባደረገው ጥብቅ እና የተቀናጀ ክትትል ከፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን እና ከሌሎች ፀጥታ አካላት ጋር በመሆን 15 የሽብር ቡድኑ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር እንዲውሉ አድርጓል።

አገልግሎት መሥሪያ ቤቱ ለመገናኛ ብዙኀን በላከው መግለጫ እንዳመለከተው፣ የተደራጀ የህቡዕ ቡድን መሥርተው እና ከሽብር አቀነባባሪዎች የውጭ ተልእኮ ተቀብለው በአዲስ አበባ በሚገኘው የተባበሩት አረብ ኢሚሬትስ ኤምባሲ ላይ የሽብር ጥቃት ለመፈጸም ሲንቀሳቀሱ የቆዩት አሸባሪዎች ለጥቃት ሊጠቀሙባቸው ያዘጋጇቸው ከፍተኛ የጦር መሣሪያዎች እና ለፍንዳታ ሥራ የሚውሉ ተቀጣጣይ ቄሳቁሶች እና የተለያዩ ሰነዶች ተገኝተዋል።

የህቡዕ ቡድኑ በአዲስ አበባው የተባበሩት አረብ ኢሚሬትስ ኤምባሲ ላይ ጥቃት ለመፈጸም የሚያስችል የቅድመ ዝግጅት፣ የጥናት እና የመረጃ ማሰባሰብ ሥራ ሲያካሂድ እንደቆየ የሚያሳዩ ተጨባጭ ማስረጃዎች መገኘታቸውን የጠቆመው መግለጫው፣ የብሔራዊ መረጃ እና ደህንነት አገልግሎት ከኅዳር 2013 ዓ.ም ጀምሮ ከሌሎች የሀገር ውስጥ እና የውጭ መረጃ ተቋማት ጋር በመሆን ጥብቅ ክትትል እና የመረጃ ልውውጥ በማድረግ የታቀደውን የሽብር ጥቃት ማክሸፍ ችሏል።

በአዲስ አበባ የተባበሩት አረብ ኢሚሬትስ ኤምባሲ ላይ የሽብር ጥቃት ለማድረስ በህቡዕ ተደራጅተው ሲንቀሳቀሱ ከነበሩት መካከል ጥቂቶቹ ከመያዛቸው በፊት በኤምባሲው ሕንፃ አካባቢ ከፍተኛ የጦር መሣሪያ ይዘው ለድብቅ ሴራቸው ሲንቀሳቀሱ እንደነበርም በክትትል መታወቁን መግለጫው አትቷል።

የሽብር ጥቃቱን ለመፈጸም ሲንቀሳቀሱ ከነበሩት መካከል የቡድኑን አባላት ሲመራ የነበረው የ35 ዓመቱ ዓሊ አህመድ አርዳይቶ ከፌዴራል ፖሊስ የወንጀል ምርመር ቢሮ ጋር በመቀናጀት በቁጥጥር ሥር እንዲውል መደረጉን መግለጫው አመልክቷል።

ለዓሊ አህመድ አርዳይቶ ለሽብር ጥቃቱ ማቀነባበሪያነት እንዲውል በዐሥር ሺዎች የሚቆጠር የአሜሪካ ዶላር እንደተላከለት ከተሰበሰቡ መረጃዎች ማረጋገጥ እንደተቻለ የጠቆመው መግለጫው፣ ከዚህ ግለሰብ ጋር ግንኙነት የነበረው እና የሽብር ጥቃት ለመፈጸም በህቡዕ ሲያሴር የቆየው መሐሙድ አብዱልቃኒ የተባለ ሌላ ተጠርጣሪም ከቀናት በኋላ በቁጥጥር ሥር በዋለበት ወቅት በመኖሪያ ቤቱ የጦር መሣሪያዎች፣ ለፍንዳት ስራ የሚውሉ ተቀጣጣይ ቄሳቀሶች እና ሰነዶች መያዛቸውን አስታውቋል።

ሌላ ተመሳሳይ ተልእኮ የተሰጠው ህቡዕ ቡድንም በሱዳን ካርቱም በሚገኘው የተባበሩት አረብ ኢሚሬትስ ኤምባሲ ላይ ተመሳሳይ የሽብር ጥቃት ለመፈጸም ዝግጅት ሲያደርግ መቆየቱን የጠቆመው መግለጫው፣ መረጃውን ቀድሞ ያገኘው እና ክትትል ሲያደርግ የቆየው የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት የግንኙነት መረቡን ለመበጣጠስ እንዲሁም ተጠርጣሪዎችን አድኖ ለመያዝም ከሱዳን የመረጃ እና የደህንነት ተቋም ጋር በቅንጅት መሠራቱን ጠቁሟል።

ለህቡዕ የሽብር ቡድኑ መሪ ከውጭ አመራር የሚሰጠው ኑሮውን በስዊዲን ያደረገው አህመድ እስማኤል የተባለ ግለሰብ ሲሆን፣ የሽብር ጥቃት ዕቅድ በማውጣት እና ከሽብር ቡድኑ አባላት ጋር ግንኙነት በመፍጠር በአዲስ አበባ የተባበሩት አረብ ኢምሬትስ ኤምባሲ የደህንነት መረጃዎች እንዲሰበሰቡ አቅጣጫ ሲሰጥ ቆይቷል።

የብሔራዊ መረጃ እና ደህንነት አገልግሎት በህቡዕ የተደራጀው የሽብር ቡድን እንቅስቃሴን በተመለከተ ከአውሮፓ፣ አፍሪካ እና እስያ የመረጃና ደህንነት ተቋማት ጋር የተቀናጀ የመረጃ ልውውጥ እና ብርቱ ክትትል በማድረግ አህመድ እስማኤል በስዊዲን ሀገር በቁጥጥር ሥር እንዲውል መደረጉን መግለጫው አመልክቷል።

በአዲስ አበባ ከተማ በሚገኘው የተባበሩት አረብ ኢሚሬትስ ኤምባሲ ሊቃጣ የነበረው የሽብር ጥቃት የከሸፈው አገልግሎት መሥሪያ ቤቱ ከውጪ እና ከሀገር ውስጥ የመረጃ እና ደህንነት ተቋማት ጋር የተቀናጀ ክትትል እና የመረጃ ልውውጥ በማደረጉ መሆኑን የጠቆመው መግለጫው፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከተቀነባበረው የሽብር ሴራ ጋር በተያያዘ ከኢትዮጵያ እና ከስዊድን በተጨማሪ በሌሎች ሀገራትም ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን አመልክቷል።

ሌሎች ከሴራው ጋር ግንኙነት ያላቸው እና በተለያዩ የዓለም ሀገራት የሚገኙ 21 ተጠርጣሪ ግለሰቦችንም በቁጥጥር ሥር የማዋሉ ተግባር ተጠናክሮ መቀጠሉን መግለጫው አመልክቷል።

በአገር ውስጥ በቁጥጥር ስር የዋሉ የሽብር ቡድኖቹ አባላትና ግብረ አበሮቻቸው በፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ወንጀል ምርምራ ቢሮ ጉዳያቸው በመጣራት ላይ እንደሚገኝ አገልግሎት መሥሪያ ቤቱ በላከው መግለጫ አስታውቋል።

የብሔራዊ መረጃ እና ደህንነት አገልግሎት ለመገናኛ ብዙሃን በላከው መግለጫ እንዳመለከተው፣ አባላትን በመመለመል፣ የሽብር እቅድ በማውጣትና ዒላማዎችን በመለየት አዲስ አበባ እና ሱዳን በሚገኙት የተባበሩት አረብ ኢሚሬትስ ኤምባሲዎች ላይ ጥቃቶችን ለመፈጸም ስምሪት ወስደው እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ የነበሩ ተጠርጣሪ የሽብር ቡድኖቹ አባላት እንዲያዙ ሲደረግ፣ ኅብረተሰቡ ያደረገው ተሳትፎም ከፍተኛ እንደነበር ጠቁሟል።

በቀጣይም ሕዝባችን ይሄን ተገንዝቦ አስፈላጊውን ጥንቃቄ እንዲያደረግ እና የተለየ ነገር ሲመለከትም በአካባቢው ላለ የፀጥታ አካል መረጃ በመስጠት የተለመደ ትብብሩን አጠናክሮ እንዲቀጥል አገልግሉት መሥሪያ ቤቱ ጥሪ ያቀርባል።