በአዲስ አበባ የተገነቡ የቱሪዝም መዳረሻዎች ከገቢ ምንጭነት ባሻገር የከተማዋ የውበት መገለጫ መሆናቸው ተገለጸ

ጥቅምት 15/2015 (ዋልታ) በአዲስ አበባ በቅርብ ዓመታት የተገነቡ የቱሪዝም መዳረሻዎች ከገቢ ምንጭነት ባሻገር የከተማዋ የውበት መገለጫ መሆናቸውን ምክትል ከንቲባ ጃንጥራር አባይ ገለጹ።

የአዲስ አበባ ከተማ የቱሪዝም ብራንድና ሎጎ “አፍሪካዊቷ መልኅቅ (The Vibrant of Africa)” በሚል ተዘጋጅቶ በዛሬው እለት ይፋ ሆኗል።
የዓለም የቱሪዝም ቀን “አዲስ እሳቤ ለቱሪዝም” በሚል መሪ ሃሳብ በዓለም ለ43ኛ በኢትዮጵያ ለ35ኛ ጊዜ በተለያዩ ዝግጅቶች በአዲስ አበባ በመስቀል አደባባይ ተከብሯል።

በመርሃ ግብሩ ላይ በመገኘት መልእክት ያስተላለፉት የከተማ አስተዳደሩ ምክትል ከንቲባ ጃንጥራር አባይ፤ ዘርፈ ብዙ አገራዊ ጠቀሜታ ያለውን የቱሪዝም ሃብት ለማሳደግ መንግስት በልዩ ትኩረት እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

ለቱሪዝም ዕድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያላቸው የተለያዩ መዳረሻ ስፍራዎች በመገንባታቸው ለሴክተሩ ተጨማሪ አቅም ሆኗል ብለዋል።
በአዲስ አበባ በቅርብ ዓመታት የተገነቡ የቱሪዝም መዳረሻዎች ከገቢ ምንጭነት ባሻገር የከተማዋ የውበት መገለጫ መሆናቸውን ምክትል ከንቲባው ተናግረዋል።
የለውጥ ጉዞው የሚታዩ ስኬቶች እየተመዘገቡበት መሆኑን ጠቅሰው በቱሪዝም ልማት በአዲስ አበባ የታየውም አስደናቂ መሆኑን ገልጸዋል።

የአዲስ አበባ ባህል፣ ኪነ ጥበብና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ ሂሩት ካሳው (ፒኤችዲ)፤ ኢትዮጵያን ተመራጭ የቱሪዝም መዳረሻ የማድረጉ ስራ በተጠናከረ መልኩ መቀጠሉን ተናግረዋል።

በጥቂት ሙዚየሞች ላይ ተንጠልጥሎ የነበረው የከተማዋ የቱሪዝም እንቅስቃሴ መንግስት በሰጠው ትኩረት በአስደናቂ ለውጥ ላይ ይገኛል ማለታቸውን የከንቲባ ጽ/ቤት መረጃ አመላክቷል።

በዚህም በከተማዋ ፓርኮች፣ አደባባዮች ፣ሙዚየሞችና ተጨማሪ ማራኪ የመስህብ ቦታዎች እንዲለሙ መደረጉ አዲስ አበባ የጎብኚዎችን ቀልብ በመሳብ የነዋሪዎቿ የኩራት ምንጭ ለመሆን መብቃቷን ገልጸዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ የቱሪዝም ብራንድና ሎጎ “አፍሪካዊቷ መልኅቅ (The Vibrant of Africa)” በሚል ተዘጋጅቶ በዛሬው እለት ይፋ ሆኗል።

የዓለምን የቱሪዝም ቀን አስመልክቶ የተዘጋጀ የቱሪዝም አውደ ርዕይ ለሦስት ተከታታይ ቀናት በመስቀል አደባባይ ለሕዝብ ክፍት ሆኖ ይቆያል።