ሰኔ 21/2013 (ዋልታ) – በአዲስ አበባ የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ መርኃግብር እና የክረምት ወራት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ስራ በክፍለ ከተሞች ደረጃ በመካሄድ ላይ ይገኛል፡፡
በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የዴሞክራሲ ግንባታ ማዕከል አስተባባሪ መለሰ ዓለሙ ችግኞችን በመትከል ለሚቀጥለው ትውልድ የለመለመች ሃገርን ለማስረከብ የተጀመረውን ተግባር በማጠናከር የበለጸገች ሃገር ለመፍጠር ጎን ለጎን ዴሞክራሲን ማጽናት ይገባል ብለዋል።
የዘንድሮን ጨምሮ ከዚህ ቀደም የተተከሉ ችግኞችን መንከባከብ እንደሚገባ የገለጹት አቶ መለሰ፣ ህብረተሰቡም በዚህ ተግባር የነቃ ተሳትፎ እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል።
የየካ ክፍለ ከተማ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ አስፋው ተክሌ በበኩላቸው፣ በክፍለ ከተማው በ2013 ዓ.ም የአረንጓዴ አሻራ መርኃግብር ከ800 ሺህ በላይ ችግኞችን ለመትከል እና በክረምት በጎ ፍቃድ አገልግሎት ከ100 በላይ የአቅመ ደካማ ቤቶችን ለማደስ መታቀዱን ገልጸዋል።
በዛሬው እለትም በክፍለ ከተማው 16 የአቅመ ደካማ ሰዎች ቤቶችን የማደስ ስራ እንደተጀመረ ከአዲስ አበባ ፕሬስ ሴክሬታሪያት ያገኘነው መረጃ አመላክቷል፡፡
በዛሬው ዕለት በየካ ክፍለ ከተማ ደረጃ የአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ መርኃግብርና የ2013 የክረምት ወራት በጎ ፈቃድ አገልግሎት በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የዴሞክራሲ ግንባታ ማዕከል አስተባባሪ መለሰ ዓለሙ፣ የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈፃሚ ኢንጅነር ዮናስ አያሌው፣ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ዴኤታ ቡዜና አልቃድር፣ የክፍለ ከተማው የስራ ኃላፊዎች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ ወጣቶች እና ልዩ ልዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ተገኝተዋል፡፡