በአዲስ አበባ የውጭ ሀገራት ጣልቃ ገብነትን የሚቃወም ሰልፍ እየተካሄደ ነው

ኅዳር 16/2014 (ዋልታ) የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ጥምረት ለኢትዮጵያ ህዝብ ያዘጋጀው “ከኢትዮጵያ ላይ እጃችሁን አንሱ!! ፤ የውጭ ጣልቃ ገብነትን አንቀበልም!!” የሚል ሰላማዊ ሰልፍ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው።

በሰልፉ ላይ የውጭ ጣልቃ ገብነትን የሚያወግዙና ምዕራባዊያን እጃቸውን ከኢትዮጵያ ላይ እንዲያነሱ የሚያሳስቡ መፈክሮች በተለያዩ ቋንቋዎች እንዲታዩ እየተደረገ ነው።

ሰልፉ መነሻውን አራት ኪሎ በማድረግ መድረሻውን የአሜሪካ እና የኢንግሊዝ ኤንባሲ እንደሚያደርግ ተገልጿል፡፡

በሰልፍ ላይ ሻማ በማብራት ጉዞ የሚደረግ ሲሆን ለ10 ደቂቃ ያክል በመላው ሀገሪቱ የሚገኙ መኪናዎች በተመሳሳይ ሰዓት ማብራት እያበሩ የጥሩንባ ድምፅ እንዲያደርጉ ይደረጋል ተብሏል።

ይህም ዋና ዓላማው ምዕራባዊያን ሀገራት የኢትዮጵያን እውነት እያዩ እና እየሰሙ አለመስማታቸውን እና አለማየታቸውን ለማስገንዘብ እንደሆነ ተመላክቷል።

በሰልፉ ላይ በአረብኛ፣ እንግሊዘኛ እና ቻይንኛ እንዲሁም ፈረንሳይኛ ቋንቋ የተፃፉ መፈክሮች እየተስተጋቡ ይገኛሉ።

በሌላ በኩል ኢትዮጵያ ለገጠማት ችግር እንደማትበገር ለማረጋገጥ ያለመ ሰልፍ ነውም ተብሏል።

በሰልፉ ላይ አባት አርበኞችን ጨምሮ የተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች ተሳታፊ ሆነዋል።

በሚልኪያስ አዱኛ