በአዲስ አበባ የግብርናና የኢንዱስትሪ ምርቶች በተመጣጣኝ ዋጋ እየቀረቡ መሆኑ ተገለጸ።

ጥቅምት 21/2014 (ዋልታ) በአዲስ አበባ ከተማ በተመረጡ ቦታዎች የግብርናና የኢንዱስትሪ ምርቶች ለህብረተሰቡ በተመጣጣኝ ዋጋ እየቀረበ ነው።
በዛሬው ዕለትም በንፋስ ስልክ ላፍቶ ጀሞ 67 ቁጥር ማዞሪያ፣ በመገናኛ፣ በፒያሳ፣ በሜክሲኮ አደባባይ እና በቃሊቲ መናኸሪያ በርካታ ነዋሪዎች የተለያዩ የግብርናና የኢንዱስትሪ ምርቶችን በመገበያየት ላይ ይገኛሉ።
በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ጀሞ 67 ቁጥር ማዞሪያ በተካሄደው ግብይት ላይ የተገኙት የከተማው ንግድ ቢሮ ኃላፊ አደም ኑሪ በከተማዋ እየታየ ያለውን የኑሮ ውድነት ለመቆጣጠር እና በምርት አቅርቦትና ስርጭት የሚፈጠረውን ሰው ሰራሽ የዋጋ ንረት መቀነስ ያስችላል ብለዋል ።
በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኙ የሸማቾች ኅብረት ስራ ማኅበራት፣ የሰብልና አትክልት አቅራቢዎች፣ የጅምላ ነጋዴዎች እና በምግብ ማቀነባበር የተሰማሩ ፋብሪካዎች እንዲሁም በአዲስ አበባ ዙሪያ የኦሮሚያ ልዩ ዞን የሚገኙ የኅብረት ስራ ማህበራትና አምራች አርሶ አደሮች ተሳትፈዋል።
በባዛሩም ከግብርና ምርቶች የጤፍ፣ የስንዴ ዱቄት፣ አትክልትና ፍራፍሬዎች የቀረቡ ሲሆን ከኢንዱስትሪ ምርቶች ደግሞ ዘይት፣ ማካሮኒና ፓስታ እንዲሁም የባልትና ውጤቶች መቅረባቸውን ከከተማ አስተዳደሩ ፕሬስ ሴክሬታሪያት የተገኘው መረጃ ያመለክታል።