በአዲስ ዋልታ የተደረጉ ለውጦችና የይዘት ማሻሻያዎች ዘመኑን የዋጁ ናቸው – ፍስሃ ይታገሱ (ዶ/ር)

ሰኔ 12/2016 (አዲስ ዋልታ) በአዲስ ዋልታ የተደረጉ ለውጦችና የይዘት ማሻሻያዎች ዘመኑን የዋጁና ፈጣን መሆናቸውን የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ዴኤታ ፍስሃ ይታገሱ (ዶ/ር) ገለጹ።

ሚኒስትር ዴኤታው በዛሬው ዕለት የዋልታ ሚዲያና ኮሙዩኒኬሽን ኮርፖሬት የስራ እንቅስቃሴን ጎብኝተዋል፡፡

በጉብኝታቸው ወቅት አዲስ ዋልታ በአጭር ጊዜ ውስጥ በርካታ ለውጥ ማሳየቱን ተናግረው የተደረጉት ለውጦችም የይዘት ማሻሻያዎችን ጨምሮ ዘመኑን የዋጁና ፈጣን መሆናቸውን አንስተዋል፡፡ ለውጦቹ ምቹና ንቁ የስራ አካባቢ የሚፈጥሩ መሆናቸውንም አድንቀዋል፡፡

ዋልታ ሚዲያና ኮሙዩኒኬሽን ኮርፖሬት ከንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ጋር ጥሩ ግንኙነት እንደነበረው ያነሱት ሚኒስትር ዴኤታው የዛሬው ጉብኝትም በቀጣይ ሁለቱ ተቋማት በጋራ የሚሰሩበትን ሁኔታ የሚያመቻች እና በመተጋገዝ ጥሩ ስራ የሚሰሩበት መሆኑን አመላክተዋል።

ሚዲያ ለሀገር ግንባታ ትልቅ አበርክቶ እንዳለውና አዲስ ዋልታም ይህንን ኃላፊነት ለመወጣት ብዙ ወጣት ባለሙያዎች ያሉበት መሆኑን መመልከታቸውን አንስተዋል፡፡

በመሆኑም የተጀመረው ሪፎርም ተጠናክሮ እንዲቀጥልና ለሀገር ግንባታና ለብሄራዊ መግባባት አበክሮ በመስራት አስተዋጽኦ እንዲያደርጉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

በማህሌት መህዲ