በአዶላ ከተማ የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ቀጥሏል

ሐምሌ 22/2013 (ዋልታ) – ዋልታ ሚዲያ እና ኮምኒኬሽን ፣ፋና ብሮድካስት እና የሁለቱ ተቋማት ጥምረት የሆነው ዋፋ በጋራ በመሆን የክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎትን በጉጂ ዞን አዶላ ከተማ በዛሬው እለትም ቀጥሏል።

በመርሀ ግብሩ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ውስጥ የሚኖሩት አቅመ ደካሞች  የመኖሪያ ቤት ግንባታ የተከናወነ ሲሆን  በዘምዘም ቀበሌ ኦዲ መኮንኒ የችግኝ ተከላ ተኳሂዷል።

የዋልታ ሚዲያ እና ኮሙኒኬሽን ኮርፖሬት ዋና ስራ አስፈፃሚ ዶክተር ንጉሴ መሸሻ ዋልታ በክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ለማህበረሰቡ  ከሚሰራቸው ስራዎች መካከል አንዱ የችግኝ ተከላ መሆኑን ገልፀው የሀገርን መርህ ከማስፈፀም አንፃር ሁሉም ሊተገብረው የሚገባ መልካም ምግባር መሆኑን ጠቁመዋል።

በአዶላ ከተማ በዘምዘም ቀበሌ በተከናወነው የክረምት ችግኝ ተከላ መርሀ ግብር ላይ ተሳታፊ የሆኑት የዋፋ ፕሮሞሽን  ምክትል ስራ  አስፈፃሚ  ሲሳይ ታደሰ ተቋማት በተባበረ ክንድ ሲሰሩ የሚያመጡት ውጤት ከፍተኛ መሆኑን ጠቁመው እህት ተቋማት የሆኑት ዋልታ ፣ዋፋ እና ፋና የዚህ መቀናጀት ተምሳሌት ናቸው ብለዋል።

በጉጂ ዞን አዶላ ከተማ በተካሄደው የ2013 የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ከ16 ሺህ በላይ ሀገር በቀል ችግኞች በስድስት ሄክታር ላይ ይተከላል ተብሎ ይጠበቃል።

(በቁምነገር አህመድ)