በአገሪቱ ዘላቂ ሰላምና መረጋጋትን ማስፈን ቅድሚያ ተሰጥቶት መሠራት እንዳለበት በጉባኤው አቋም መያዙ ተገለጸ

መጋቢት 5/2014 (ዋልታ) በብልጽግና ፓርቲ ጉባኤ በአገሪቱ ዘላቂ ሰላምና መረጋጋትን ማስፈን ቅድሚያ ተሰጥቶት መሠራት ያለበት እንደሆነ አቋም ተይዞበት አቅጣጫ መቀመጡን የፓርቲው ዓለም ዐቀፍና ሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ቢቂላ ሁሪሳ (ዶ/ር) ገለጹ።

የብልጽግና ፓርቲ ለሦስት ቀናት ሲያካሂድ የነበረውን ጉባኤ መጠናቀቅን አስመልክቶ ለመገናኛ ብዙኃን መግለጫ የሰጡት ኃላፊው ፓርቲው በተለያዩ ጉዳዮች ላይ መክሮ አቋም በመያዝ፣ ውሳኔ በማስተላለፍና አቅጣጫ በማስቀመጥ ማጠናቀቁን አስታውቀዋል።

ብልጽግና የመጀመሪያውን ጉባኤ በተሳካ ሁኔታ ማጠናቀቁን የገለፁት ቢቅላ ()ዶ/ር ጉባኤው በያዛቸው ሦስት ዓላማዎች ዙሪያ መክሮ የጋራ አቋም በመያዝ ማጠናቀቁ ታሪካዊ ያደርገዋልም ብለዋል።

ኢትዮጵያን በዲፕሎማሲ ረገድ ስኬታማ ማድረግ ላይ የመከረው ፓርቲው በቀጣይ ጠንካራ ሥራዎችን በመሥራት አሁን ላይ የታየውን የተስፋ ጭላንጭል ወደ ተግባር መቀየር እንዳለበት አቅጣጫ ተቀምጧልም ነው ያሉት።

የብልጽግና ፓርቲ አመራሮችና አባላት አካታች አገራዊ ምክክሩ እንዲሳካ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ትብብር እንዲጠናከር፣ የዴሞክራሲ ሥርዓት ሪፎርም ማስቀጠል ላይ፣ ኢትዮጵያዊ አንድነትን ማጠናከርና ብዝኃነትን የሚያከብር አንድነት መገንባት ላይ መስራት እንዳለባቸውም ከስምምነት ተደርሷል ብለዋል።

ፓርቲው በጉባኤው የተመለከተው ሌላኛው ጉዳይ የኢኮኖሚ ጫናን መቀነስ ላይ አፋጣኝ ርምጃ መወሰድ መሆኑን ጠቅሰው በዚህም ከስምምነት መደረሱን አመልክተዋል።

ዘላቂ የኢኮኖሚ ጥያቄን መመለስ ላይ ጠንካራ ኢኮኖሚን መገንባት እና የዜጎች ኑሮን ማሻሻል ላይ መሠራት አለበትም ተብሏል።

ጉባኤው የአገር ሉዓላዊነት ማስከበር ላይም ተቀናጅተን መስራት አለብን ሲል አቅጣጫ አስቀምጧል ነው ያሉት።

ፓርቲው በቀጣይ ዜጎችን በማስተባበር እና የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር በመቀናጀት የመቻቻል፣ የመከባበር፣ የመተጋገዝ መንፈስ እና ማኅበራዊ እሴትን የሚያጠናክር ሥራን መስራት አለበት የሚለው በአንክሮት የታየ ጉዳይ ነው ሲሉም ቢቂላ (ዶ/ር) ተናግረዋል።

ለዚህም የፓርቲው አባላት ሕዝብን ለማገልገል ያላቸውን ቁርጠኝነት አሳይተዋል፤ ለዚህ መሳካትም ኅብረተሰቡ የሚጠበቅበትን በመወጣት እንዲያግዘው ፓርቲው ጥሪውን ያቀርባል ብለዋል።

በአስታርቃቸው ወልዴ