በአፍሪካ ትልቋ የስንዴ አምራች መሆን የቻለችው ኢትዮጵያ

ሰኔ 16/2015 (ዋልታ) የአፍሪካ ምሥራቃዊው ቀጣና በአስቸጋሪ ሁኔታዎች ሲገለፅ ሰርክ ቢታወቅም በፈተናዎች መካከል የምጣኔ ሀብት እመርታዎችም በከፍተኛ መጠን እየተመዘገቡ እንደሚገኙ የዓለም ባንክ እና የሌሎች ተቋማት ሪፖርቶች ይጠቁማሉ።

በቤልጂየም የኬንያ አምባሳደር የሆኑት አምባሳደር ቢታንጊ ንዲሞ ሰሞንኛዎቹን ዓለም አቀፍ ኢኮኖሚያዊ ሪፖርቶች መሠረት በማድረግ በቢዝነስ ዴይሊ ላይ ባቀረቡት ሐተታዊ ጽሑፍ “ከሰሃራ በታች የሚገኙ የአፍሪካ ሀገራት በምጣኔ ሀብታዊ ግስጋሴው ረገድ የጦፈ ውድድር ላይ ናቸው” ብለዋል።

“በተለይም ኢትዮጵያ እና አንጎላ ከናይጄሪያ እና ደቡብ አፍሪካ በመቀጠል ሦስተኛው ባለ ግዙፍ ኢኮኖሚ ለመሆን ኬንያን ተገዳድረዋል” በማለት በዓለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅት (IMF) የተረጋገጡ ያሏቸውን አሐዞች በአስረጂነት አጣቅሰዋል።

በዚህም አይ.ኤም.ኤፍ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ዕድገትን በ13.5 በመቶ የማደግ ትንበያ ማስቀመጡን ነው የጠቆሙት።

አምባሳደሩ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚያዊ ሁኔታ በዳሰሱበት የመጣጥፋቸው ክፍል “የሀገሪቱ ምጣኔ ሀብት የተለያዩ የዘርፍ ስብጥሮችን ያቀፈ ሆኖ መገኘቱን ጠቅሰዋል። በዚህም የአገልግሎት ዘርፉ ከጠቅላላው የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምርት 36.8 በመቶ፣ ግብርና 35.5 በመቶ እና ኢንዱስትሪው 23.11 በመቶ ድርሻ መያዛቸውን ነው የገለጹት።

በተለይም የኢትዮጵያ አየር መንገድ የካርጎ እና የሎጂስቲክስ አገልግሎት በአፍሪካ ወደር አልባ የትራንስፖርት መሠረተ ልማትን እውን በማድረግ አስደናቂ ስኬት አስመዝግቧል ብለዋል።

በቅርቡ በኢትዮጵያ የተጀመረው የቴሌኮም ዘርፍን ለግል ኩባንያዎች ክፍት የማድረግ እርምጃ ውጤታማነቱን ያሳድጋል ያሉት በቤልጂየም የኬንያው አምባሳደር ኢትዮጵያ በስንዴ ምርት ረገድ ያስመዘገበችውንም ውጤት ጠቅሰውታል። በዚህም ሀገሪቱ በአፍሪካ ትልቋ የስንዴ አምራች ለመሆን መብቃቷን እና በተለይ ደግሞ በሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነት በተከሰተው የስንዴ አቅርቦት ቀውስ ወቅት ለሌሎች ሀገራት ምግብ አቅራቢ ለመሆን አስችሏታል ነው ያሉት።

ከዚህ በተጨማሪም የኢትዮጵያ የማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ በተለይም ከቻይና ኩባንያዎች ጋር በመተባበር በቆዳ እና ጨርቃጨርቅ ዘርፉ ዕድገት በማስመዝገብ ላይ መሆኑን ጠቁመው ይህም የጦርነት ፈተናዎች ቢኖሩበትም የኢትዮጵያ የኢኮኖሚያዊ ዕድገት ቀመር ውጤታማ መሆኑ እየታየ ነው ብለዋል አምባሳደሩ።

የአንጎላን ኢኮኖሚ የተመለከተው ይኸው መጣጥፍ ሀገሪቱ ከአፍሪካ ትልቋ የነዳጅ ዘይት አምራቾች መካከል እንደመሆኗ ከጠቅላላ የሀገር ውስጥ ምርቷ ውስጥ የነዳጅ ዘርፉ ከፍተኛውን ድርሻ ቢይዝም ሀገሪቱ ያሏትን እንደ አልማዝ፣ የታዳሽ ኃይል (ሃይድሮ) እና እንደ ግብርና ባሉ ዘርፎች ያልተጠቀመችበት እምቅ አቅም እያላት በነዳጅ ላይ ብቻ ማተኮሯ ኢኮኖሚዋ በዓለም አቀፍ የነዳጅ ዋጋ ተፅዕኖ ስር እንዲውል ያደርግባታል ብለዋል።

አንጎላ ከግዙፍነቷና ካላት እምቅ ሀብቷ አንፃር ትልቅ የኢኮኖሚ ተዋናይ መሆን ብትችልም የሰው ኃይል እጥረት ኢኮኖሚዋን ከሌሎች የአፍሪካ ሀገራት አንፃር ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ ተግዳሮት ፈጥሮባታል ይላሉ።

ኢቢሲ ቢዝነስ ዴይሊን ዋቢ አድርጎ እንደዘገበው በአይ.ኤም.ኤፍ ሪፖርት መሠረት የኬንያ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት በኮቪድ-19፣ በድርቅ እና በዓለም አቀፍ የግብይት ሰንሰለቶች መስተጓጎል ተፈትኗል ያሉት አምባሳደሩ በዚህም የዕድገት ምጣኔ ትንበያው 2.4 በመቶ እንዲሆን ገድቦታል ይላሉ።

በአንፃሩ የዓለም ባንክ ሪፖርቶች ከነዚህ አሐዞች የተለየ መሆኑን የሚናገሩት አምባሳደር ቢታንጊ ባንኩ ያስቀመጠው የኬንያ ዕድገት ምጣኔ አምስት በመቶ መሆኑን ይጠቁማል።