በኢትዮጵያ፣ ኬኒያና ሶማሊያ ተግባራዊ የሚደረግ የከርሰ ምድር ውሃ ፕሮጀክት ይፋ ሆነ

መስከረም 12/2015 (ዋልታ) በኢትዮጵያ፣ ኬኒያና ሶማሊያ ተግባራዊ የሚደረግ የከርሰ ምድር የውሃ ልማት ፕሮጀክት ይፋ ሆነ።

ፕሮጀክቱ የምስራቅ አፍሪካ የከርሰ ምድር የውሃ ልማት ሲሆን በዓለም ባንክ በተገኘ ድጋፍ ተግባራዊ የሚደረግ መሆኑም ታውቋል።

የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ሀብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር)፣ የመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስትር አይሻ መሀመድን እንዲሁም የዓለም ባንክ የምስራቅና መካከለኛው አፍሪካ ቀጣና ዳይሬክተር ሶማ ጎሆሽ ሞውሊክ በአዲስ አበባ ይፋ በተደረገው መርኃ ግብር ላይ ተገኝተዋል።

የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ሀብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር) ፕሮጀክቱ የምስራቅ አፍሪካን የከርሰ ምድር ውሃ በአግባቡ በማልማት ለቀጣናው ዘላቂ ልማትና የውሃ አጠቃቀም እንደሚያግዝ ገልፀዋል።

ፕርጀክቱ በሚተገበርባቸው ወረዳዎች ለአነስተኛ መስኖና የመጠጥ ውሃን ከማሻሻል ባሻገር ለቀጣናው መረጃ ልውውጥና ድንበር ተሻጋሪ የውሃ ስራ አመራርን ለማሻሻል እንደሚያግዝም አመልክተዋል።

ፕሮጀክቱ በኢትዮጵያ በሁሉም ወረዳዎች በአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖ እየተፈተኑ ላሉ ቆላማ አካባቢዎች ሁነኛ አማራጭ ስለመሆኑ አንስተው በኢትዮጵያ ከ8 ሚሊዮን ህዝብ በላይ ከከርሰ ምድር ውሃ እንደሚጠቀም አውስተዋል።

የከርሰ ምድር ውሃ 60 በመቶውን የኢትዮጵያ ውሃ አቅርቦት ቢሸፍንም በአግባቡ አልተጠቀንምበትም ያሉት የመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስትሯ አይሻ መሀመድ ፕሮጀክት የከርሰ ምድር ውሃ ዘላቂነት ባለው መልኩ ለመምራትና ለመጠበቅ እንደሚያግዝ ጠቁመዋል፡፡

በኢትዮጵያ ባለፈው ዓመት ከ1 ነጥብ 5 ሚሊዮን የቤት እንስሳት በድርቅ መሞታቸውን ገልፀው በ55 ወረዳዎች ላይ የሚተገበረው ይህ ፕሮጀክት በአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖ ውሃ በማጣት ለስደትና ችግር የሚጋለጡ ወገኖችን ለመታደግ እንደሚያስችል ተናግረዋል።

የ210 ሚሊየን ዶላር በጀት የተያዘለት የውሃ ልማት ፕሮጀክቱ ለሰዎችና የእንስሳት ውሃ መሰረተ ልማት በመዘርጋት ቀጣናዊ ትስስር ለማጎልበት እንዲሁም ለአገራዊ ዕቅዶችና ዘላቂ ልማት ግቦች ስኬት ትልቅ ሚና ይኖረዋል ብለዋል።

በድርቅ ተጎጂ አካባቢዎች ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት እንደሚሰራ ገልፀው የወቅቱ የከርሰ ምድር ውሃ አጠቃቀም በቅጡ ለመምራትና ለመጠቀም ለማህበራዊና የኢኮኖሚ ዕድገት ያግዛልም ነው የተባለው።

በዓለም ባንክ ለምስራቅና መካከለኛ አፍሪካ ቀጣና ዳይሬክተር ሶማ ጎሆሽ ፕሮጀክቱ በኢትዮጵያ፣ ኬኒያና ሶማሊያ ተግባራዊ የሚደረግ መሆኑን ተናግው በዚህም ለመጀመሪያው የፕሮጀክት ክንውን ኢትዮጵያ 210 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ እንዳገኘች ገልፀዋል።

ከነዚህ አገራት ቀጥሎም ደቡብ ሱዳንና ጅቡቲ የከርሰ ምድር ውሃ ተጠቃሚ የሚያደርግ ፕሮጀክት እንደሚተገበር ገልፀዋል።

ኢትዮጵያ የገፀ ምድር ውሃ ቢኖራትም ስርጭቱ ወጥነት የሌለውና ለጎርፍ እንደሚዳረግ ገልፀው ተቋማዊ ስራዎቾን በማጠናከር የከርሰ ምድር ውሃን ማልማት ወሳኝ ነው ብለዋል።

በፕሮጀክት በ55 ወረዳዎች ላይ የውሃ ፕሮጀክቶች በመገንባት ከ1 ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ የድርቅ ተጋላጭ ወገኖች በመስኖ አገልግሎቶን በማስፋፋት ተጠቃሚ ያደርጋል፤ መፈናቀልንም ያስቀራል ነው ያሉት።

ግብርና ምርታማነትን ማሳደግ በተለይም ለቁም እንስሳት ሀብት ልማትና የሰው ሀብት ልማት አዎንታዊ ሚና ይኖረዋል ነው የተባለው።

በሌላ በኩል ለከርሰ ምድር ውሃ ጥናትና ስራ አመራር የሚያጠና ተቋማዊ አቅም ለመንገባት፣ ከቀጣናው አገራት ትስስርና ትብብር ለማጠናከር ያስችላል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።