በኢትዮጵያ ህልውና ላይ የተነሳውን ጁንታ እስከ መጨረሻው ለመደምሰስ የወጣቱ ተሳትፎ ወሳኝ ነው – ብርጋዲየር ጀነራል ተፈራ ማሞ

ብርጋዲየር ጀነራል ተፈራ ማሞ

ሐምሌ 17/2013 (ዋልታ) – በኢትዮጵያ ህልውና ላይ የተነሳውን ጁንታ እስከ መጨረሻው ለመደምሰስ ከወጣቱና ከህዝቡ የበለጠ አስተዋጽኦ ይጠበቃል ሲሉ የአማራ ክልል ልዩ ሃይል ዋና አዛዥ ብርጋዲየር ጀነራል ተፈራ ማሞ አሳሰቡ።

ዋና አዛዡ ዛሬ በሰጡት መግለጫ እንዳመለከቱት የኢትዮጵያ ጠላት የሆነው አሸባሪው ህወሃት በአስከሬን ላይ ተረማምዶ እስከ ሲኦልም ቢሆን ገብቶ ሃገር ለመበታተን ጦርነት በማካሄድ ላይ ይገኛል።

ጀግናው መከላከያ ሰራዊት፣ የየክልሎቹ ልዩ ሃይሎችና የአማራ ሚሊሻ አባላት የጁንታውን ወረራ ለመመከት ግንባር ላይ እየተፋለሙ መሆናቸውን ገልፀዋል።

በኢትዮጵያ ህልውና ላይ የተነሳውን ጁንታ እስከ መጨረሻው ለመደምሰስ ከወጣቱና ከህዝቡ የበለጠ አስተዋጽኦ እንደሚጠበቅ ተናግረዋል።

“የአሸባሪ ቡድኑን የሴራ ፖለቲካ ሙሉ በሙሉ ለማክሸፍ እየተደረገ ባለው የተቀናጀ ጥረት ሁሉም አካባቢውን ነቅቶ ከመጠበቅ በዘለለ ከሰራዊቱ ጎን በመሰለፍ ማገዝ ይገባል” ብለዋል።

የክልሉ ልዩ ሃይልና ሚሊሻም ከሌሎች አጋር ልዩ ሃይሎች እንዲሁም ከመከላከያ ሰራዊት ጎን ሆኖ አገር የማዳን ስራውን ካለፉት 8 ወራት ጀምሮ በጥንካሬ እየተወጣ መሆኑን ብርጋዴል ጀነራሉ አስታውቀዋል።

ወጣቱ የጁንታውን እኩይ ሴራ በመረዳት ወደ ስልጠና እየገባ ሲሆን ሁሉም አገሩንና ህዝቡን የማዳን የህልውና ዘመቻውን በብዛት እንዲቀላቀልም አሳስበዋል።

የህወሃት ዓላማ ሃገር እየዘረፈ ማጓጓዝ ሲሆን የመጨረሻ መዳረሻው ደግሞ እርሱ የማይመራት ኢትዮጵያ እንድትፈርስ መስራት መሆኑንም አብራርተዋል።

ዋናው የወያኔ መሳሪያ ጉልበት ሳይሆን ያልያዘውን ያዝኩ፣ ያልማረከውን ማረክሁ፣ ያላደረገውን አደረክሁ የሚለው የተለመደና ያደገበት ፕሮፖጋንዳ በመሆኑ ህዝቡ ይህንኑ የሃሰት ወሬ መረዳት እንዳለበትም ጠቁመዋል።

አሁን አሸባሪ ቡድኑ እየተጠቀመበት ያለው ስልት የትግራይን ህፃናትና ወጣቶች በገፍ ወደ ጦርነት መማገድ መሆኑን ጠቅሰዋል “የትግራይ ወንድም ህዝብም በልጆቹ ሞት እየቀለደ ያለውን ቡድን በቃህ ሊለው ይገባል” ሲሉም ጥሪ አቅርበዋል።

”የትግራይ ህዝብ የነገ እድሉ ከኢትዮጵያ ህዝብ ጋር ነው” ያሉት ዋና አዛዡ ወያኔ ለጦርነት የሚያቀርባቸውን ህፃናት፣ ሴቶችና ወጣቶች ሊከላከልና ለኢትዮጵያዊነቱ ሊቆም እንደሚገባም ገልፀዋል።

መላው የኢትዮጵያ ህዝብ ለፀጥታ ሃይሉ ስንቅ በማቅረብና ሞራል በመስጠት የሚያደርገውን ድጋፍም አሸባሪ ቡድን ሙሉ በሙሉ እስኪደመሰስ አጠናከሮ መቀጠል እንዳለበት ማሳሰባቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

ህወሓት በኢፌዴሪ ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አሸባሪ ተብሎ መፈረጁ የሚታወቅ ነው፡፡