በኢትዮጵያ እና በቻይና ልማት ባንክ መካከል ያለው ትብብር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተገለፀ

ግንቦት 9/2014 (ዋልታ) በቻይና የኢትዮጵያ ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር ተሾመ ቶጋ ከቻይና የልማት ባንክ የአሜሪካና አፍሪካ ዓለም ዐቀፍ ትብብር ዲፓርትመንት ጄኔራል-ማናጀር ቢያን ሺዩዋን ጋር በዌቢናር ተወያይተዋል።

በውይይቱ በኢትዮጵያና በባንኩ መከካል ያለው ትብብር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተገልጿል።

የኮቪድ-19 ወረርሽኝና በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል የተከሰተው ጦርነት በሀገሪቱ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ላይ የራሱን አሉታዊ ተፅዕኖ ያሳደረ ቢሆንም ኢኮኖሚው ይህን ጫና ተቋቁሞ በማደግ ላይ የሚገኝና ተስፋ ሰጪ መሆኑን አምባሳደ ተሸመ ገልጸዋል፡፡

ባንኩ በሂደት ላይ ላሉ የልማት ፕሮጀክቶችና ለሀገሪቱ የፋይናንስ ፖሊሲ ተቋማት የሚያደርገውን ድጋፍ በሀገሪቱ ቀጣይ የአስር ዓመት የልማት ዕቅድና በ8ኛው የቻይና አፍሪካ ትብብር ፎረም የሚኒስትሮች ኮንፈረንስ የልማት ትብብር ግቦች መሰረት አጠናክሮ እንዲቀጥልም ጥሪ አቅርበዋል።

ቢያን ሺዩዋን በበኩላቸው ባንኩ እ.ኤ.አ ከ2007 ጀምሮ የኢትዮጵያ ቁልፍ የልማት አጋር ሆኖ የቀጠለና ከሀገሪቱ የፋይናንስና የልማት ተቋማት ጋርም መልካም ትብብር ያለው መሆኑን ተናግረዋል።

የኢምባሲው መረጃ እንዳመለከተው ባንኩ ከኢትዮጵያ ጋር በሁለትዮሽና በባለብዙ ወገን የትብብር ዘርፎች ያለውን ግንኙነት አጠናክሮ ለመቀጠል ዝግጁና ቁርጠኛ መሆኑን ገልፀዋል።

ለፈጣን መረጃዎች፦
ፌስቡክ https://bit.ly/3Ma7QTW