በኢትዮጵያ እና ኤርትራ በድንበር አካባቢ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱን ዳግም ለማስጀመር ተስማሙ

ዶክተር አብርሃም በላይ

መጋቢት 17/2013 (ዋልታ) – በኢትዮጵያ እና ኤርትራ በድንበር አካባቢ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱን ዳግም ለማስጀመር ከስምምነት መደረሱ ተገለጸ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በኤርትራ ያደረጉትን ይፋዊ ጉብኝት አጠናቀው ተመልሰዋል፡፡

በጉብኝቱ የተሳተፉት የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትሩ ዶክተር አብርሃም በላይ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድና የኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳይያስ አፈወርቂ በሁለቱ አገራት የጋራ እና ቀጣናዊ ጉዳዮች ዙሪያ መክረዋል ብለዋል።

የትግራይ እና የኤርትራ የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነትን ለማጠናከር በቀጣይ ሊሰሩ በሚገባቸው ጉዳዮች ላይ ስምምነት መደረሱንም ዶ/ር አብርሃም ገልጸዋል።

በሁለቱ ሕዝቦች መካከል ያለውን ለዘመናት የነበረ ወንድማዊ ግንኙነት ከማጠናከር ባለፈ በመሰረተ ልማት ስራዎች ለማስተሳሰርም ከስምምነት ላይ ተደርሷል ነው ያሉት።

በዚህም በቀጣይ በጋራ ሊሰሩ የሚችሉ ፕሮጀክቶች ተቀርፀው ወደ ስራ ለመግባትም ከመግባባት ላይ ተደርሷል።

በትግራይ ክልል በነበረው የህግ ማስከበር ዘመቻ ድንበር አካባቢ ችግር እንዳይፈጠር ወደ ኢትዮጵያ ገብተው የነበሩ የኤርትራ ወታደሮችን ኤርትራ ከኢትዮጵያ ድንበር ለማስወጣት መስማማቷም ተገልጿል። ቦታውንም የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት እንዲቆጣጠረው ከስምምነት ተደርሷል ብለዋል።

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የተመራው ልዑካን ቡድን ቆይታ ስኬታማ መሆኑንም ዶ/ር አብርሃም በሰጡት መግለጫ ተናግረዋል።

(በአስታርቃቸው ወልዴ)